Fana: At a Speed of Life!

የብልፅግና ፓርቲ የፌደራል እና ክልል አቀፍ የአመራሮች ሥልጠና በተለያዩ ከተሞች መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የፌደራል እና ክልል አቀፍ የአመራሮች ሥልጠና በዛሬው እለት በተለያዩ ክልሎች መካሄድ ጀመረ።

በፌረደራል ደረጃ በአዲስ አበባ መካሄድ የጀመረው ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፥ ስልጠናው ሃገራዊ ለውጥና ከለውጡ ጋር ተያይዞ በተወሰዱ እርምጃዎች በተገኙ ስኬቶችና የቀጣይ እንቅፋቶች ላይ አመራሩ የተግባር አንድነት እንዲኖረው ለማድረግ ታልሞ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ስልጠናው የፓርቲው ፕሮግራሞችና አካሄድ ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲያዝ ያግዛል ብልዋል።

አመራሩ ከስልጠናው በኋላ የሚያገኘውን ሙሉ አቅም ተጠቀሞ በየደረጃው ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚያስችል አቅም ለመገንባትና ለቀጣይ ሀገራዊ ተልዕኮ ለማዘጋጀት ያግዛልም ብለዋል።

አሁን የምንገኝበት ጊዜ ድርብ ሀላፊነት የምንወስድበትና ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ዳግም ሀላፊነት የምንወስድበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በተያያዘ ስልጠናው በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማን ጨምሮ በሰንዳፋ፣ አዳማ እና ባቱ ከተሞች መካሄድ ጀምሯል።

በጅማው ስልጠና ላይም ከጅማ ከተማ፣ ከጅማ ዞን፣ ከቄለም ወለጋ፣ ከምእራብ ወለጋ፣ ከኢሉአባቦር እና ከቡኖ በደሌ የተውጣጡ ከ2 ሺህ 300 በላይ አመራሮችች እየተሳትፉ ነው።

ለ13 ቀናት የሚካሄደው ይህ ስልጠና በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞችም ዛሬ ተጀምሯል።

በተመሳሳይ ስልጠናው በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልልም በ14 ማዕከላት እየተሰጠ መሆኑን የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ሥልጠናው የሚሰጥባቸው ማዕከላትም ቦንጋ፣ ተርጫ፣ ጂንካ፣ ሣውላ፣ አርባምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሆሳዕና፣ ዎራቤ፣ ወልቂጤ፣ ዱራሜ፣ ሀላባ፣ ዲላ እና ሀዋሣ መሆናቸውም ተገልጿል።

በተጨማሪም በአዲስ አበባ፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ መካከለኛ እና ጀማሪ አመራር ስልጠና በዛሬው እለት መካሄድ ጀምሯል።

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንሪባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ባስተላለፉት መልእክት፥ አመራሩ ህዝብን ለማገልገልገል ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛና ዝግጁ መሆን አለበት ብለዋል።

አዲስ አበባን እንደስሟ አዲስ እናደርጋለን ስንልም በህብረትና በቅንጅት ህዝብን ማገልገል ስንችል ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በአፋር ክልልም የአፋር ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራር ስልጠና በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች በዛሬው እለት መካሄድ ጀምሯል።

ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ቀጥሎ በሚካሄደው ስልጠና ላይም በዋናነት ትኩረት የሚደረገው የመደመር እሳቤ እና የብልፅግና ፓርቲ መሠረታዊ አስተሳሰቦች ምንነትና ይዘት ላይ እንደሚሆን ታውቋል።

በነፃነት ጀማል፣ አዳነች አበበ እና በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.