Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ በአማራና አፋር ክልሎች የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብቶችና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ጥሰቶች ላይ ያደረገውን ምርመራ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ እና አፋር ክልሎች የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብቶች እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ጥሰቶች ላይ የተደረገውን ምርመራ ይፋ እያደረገ ነው።

የምርመራ ውጤቱ ከዚህ ቀደም ኢሰመኮ ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ፅህፈት ቤት ጋር በመሆን በትግራይ ክልል የተከሰተውን ጦርነት ምክንያት በማድረግ በጋራ ካወጡት ሪፖርት የቀጠለ መሆኑን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ገልፀዋል።

ሪፖርቱ ከመስከረም እስከ ታህሳስ 2014 በአፋር እና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ በቆየው ጦርነት የደረሰውን የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ችግሮችን ተመልክቷልም ነው የተባለው።
በአፈወርቅ አለሙ።

 

ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል እንደገለጹት፥ በአፋር ክልል ሶስት ዞኖች፣ በአማራ ክልል አምስት ዞኖች እና በትግራይ ክልል ደቡብ ምስራቅ ዞን እንደርታ ወረዳ የደረሱ ጉዳቶችን በ29 አባሎች ምርመራ ተደርጓል፡፡

በአፋር እና አማራ ክልሎች በተደረገ ምርመራ ሆነ ተብለው የተፈፀሙትን ህገወጥ ግድያዎች ሳይጨምር በጦርነት ውስጥ በሲቪሎች ላይ በደረሰው አደጋ ቢያንስ 403 ሰዎች ለሞት እንዲሁም 309 ለቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መዳረጋቸውንም አብራርተዋል፡፡

የጣምራ ሪፖርቱን ምክረ ሃሳቦች ለማስፈጸም የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ጨምሮ የሌሎች ሀገራዊ ተቋማት ሚና አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ዳንኤል፥ “በቀዳሚነት በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች እና ኃይሎች በአባላቶቻቸው እና አመራሮቻቸው ለተፈጸሙ ከባድ የመብት ጥሰቶች ኃላፊነት መውሰድ እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ግዴታቸውን መወጣት ለፍትሕ፣ ለእውነት፣ ለተጎጂዎችና ለተጎጂዎች ቤተሰቦች የማይታለፍ እርምጃ መሆኑን በድጋሚ ሊታወስ ይገባል” ብለዋል።

አክለውም “ከአስራ አምስት ወራት በላይ የዘለቀው ጦርነት ከዚህ የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም አድርገው ለፖለቲካዊ መፍትሔ ንግግር መጀመር ይገባቸዋል” ያሉት ዶ/ር ዳንኤል፥ በሪፖርቱ የተካተቱን ምክረ ሃሳቦች የመተግበሩ ሂደት በአፋጣኝ እንዲጀመር ለሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ጥሪ አቅርበዋል።

በአፈወርቅ አለሙ እና በተስፋዬ ከበደ

 

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.