Fana: At a Speed of Life!

ብልፅግና ፓርቲ መደመርን እንደመንገድ ብልፅግናን እንደመዳረሻ የወሰደ፣ በሀገር በቀል ሀሳብ ራሱን የተከለ መሆኑን የፓርቲው ፕሬዚዳንት ገለፁ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልፅግና ፓርቲ መደመርን እንደመንገድ ብልፅግናን እንደመዳረሻ የወሰደ፣ በሀገር በቀል ሀሳብ ራሱን የተከለ መሆኑን የፓርቲው ፕሬዚዳንት እና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ።

የብልፅግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ “ከፈተና ወደ ልዕልና!” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ በይፋ ዛሬ ተጀምሯል።

የፓርቲው ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጉባኤው መክፈቻ ንግግራቸው፥ ብልፅግና በኢትዮጵያ ታሪክ ከዚህ በፊት ከነበሩ ፓርቲዎችና ድርጅቶች በቁጥርም፥ በአደረጃጀትም፥ በሀሳብም የተለየ ፓርቲ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ፓርቲው ከ11 ሚሊየን በላይ አባላት ያሉት መሆኑን አንስተው÷ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በዚህ የአባላት ቁጥር ልክ ግዙፍ ፓርቲ የለም ብለዋል፡፡

ብልፅግና ፓርቲ የትናንቱን እሴት ሳያፈርስ፤ የነገው ብሩህ ተስፋ ፓርቲ መሆኑንም የፓርቲው ፕሬዚዳንት ገልፀዋል።

ፓርቲው ብልፅግናን በኢትዮጵያ ምድር ለማረጋገጥ የሃሳብም፣ የቁጥርም፣ የአደረጃጀትም ብቃት ያለው ፓርቲ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ የዚህ ፓርቲ አባል በመሆናችን እጅግ ኩራት ይሰማናል ነው ያሉት ፡፡

ህዝባችንን እያማረሩ ያሉትን ሌብነትንና የኑሮ ውድነትን ለማስወገድ ብልፅግና ቆርጦ የተነሳ መሆኑን ጠቁመው፥ አመራሮች ከሕዝብ ጋር ተቀራርበን የህዝብ ችግሮችን በመፍታት፥ የምንመራ ብቻ ሳንሆን ሕዝብን የምናገለግል መሆን አለብን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የምናውቃቸው ፓርቲዎች 90 በመቶ ኦሮሞ፣ 1 ወላይታ፣ 1 ጋምቤላ፣ 1 ሲዳማ ይዘው ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲ ነን ይሉ እንደነበር ጠቅሰው፥ በዚህ በአንደኛው ጉባኤያችን ላይ ብልፅግና ን የምናየው ሁሉም ብሄሮች በሚገባቸው ቁጥር ልክ የሚሳተፉበት ፓርቲ መሆኑን ነው ብለዋል።

“ዛሬ ግን የብልፅግና ፓርቲ ሁላችሁም እንደምታውቁት ከሁሉም ብሄር፤ ከሁሉም አካባቢ በቂ የሆነ ውክልና ያለው የይስሙላ ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ሳይሆን፥ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ሆኖ ሁሉን ሰብስቦ፥ ኢትዮጵያን መስሎ፥ ኢትዮጵያን ሊያበለጽግ የመጣ ፓርቲ ስለሆነ ከእስካሁኖቹ በእጅጉ የሚለይና በሚያመጣውም ውጤት በታሪክ ውስጥ በአሻራ የሚታወስ ይሆናል” ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ውስጥ ቅንጅት፣ ህብረት፣ ኢህአዴግ እንዲሁም በደርግ ጊዜ የነበሩ ፓርቲዎች ለመሰብሰብ ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ ቀርቶ በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ በርከት ያሉ ፓርቲዎች በአንድ ፕሮግራም ስር እና በኢትዮጵያ ጥላ ስር ተሰባስበው አንድ የሆኑበት የመጀመሪያው ፓርቲ ብልፅግና መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ብልፅግናን ካዩ በኋላም ሌሎች ለመከተል ድፍረት ያጡ መኖራቸውን ጠቁመው÷ ብልፅግና ፓርቲ ብዙ ቋንቋ፣ ብዙ ሕዝብ አጋርና ዋና የሚባለውን ከፋፋይ ግንብ ያፈረሰ የቀደመውን ሁሉ ያልናደ፥ ለነገ ደግሞ ብሩህ ተስፋ የሰነቀ ፓርቲ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ብልፅግና በብዙ ፈተናዎች ውስጥ የቆየ ፓርቲ ቢሆንም÷ የህዝባችንን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በህዝበ ውሳኔ በሲዳማ፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ ማረጋገጥ የቻለ ዴሞክራሲያሲያዊ ፓርቲ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ገና ብዙ ሊሠራበት የሚገባ ቢሆንም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚባል እና መራጩ ህዝብ እኩለ ሌሊት ጭምር ካርዴን ከኮሮጆ ሳላቀላቅል አልሄድም ያለበትን ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማረጋገጥ የቻለ ፓርቲ እንደሆነም ተናግረዋል።

ሰላም ለአገራችን ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ ለሰላም፣ ለልማትና ለዲሞክራሲ እንድንሰራ አደራ እላለሁ ብለዋል የፓርቲው ፕሬዚዳንት።

ከፈተና ወደ ልዕልና ስንል ከወጀብ፣ ከአውሎ ንፋስ እና ከመሬት ስበት ከሁሉም ልቆ ከፍ ብሎ ያሰበውን ራዕይ ማሳካት የሚችል ፓርቲ መሆን መቻል ማለታችን ነው ብለዋል፡፡

ዓላማችን ጠንካራ ፓርቲ፥ በእሱም የሚከወን ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት እንዲሁም ሌብነትን የሚጠየፍ ለህዝብ እፎይታ የሆነ ለህዝብ የቀረበ ፓርቲ መሆን ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ኅብረ ብሔራዊትን የሚያጠናክር፣ ሁሉም ብሔሮች እና ቋንቋዎች ተከብረው የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ የፓርቲው ዓላማ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የገጠሙንን ፈተናዎች ለመሻገር በጉልበት ብቻ ሳይሆን ጉልበት እና ስሜትን አጣምረን እንሰራለንም ነው ያሉት ፡፡
ብልፅግና እንደ ዓሳ በውሃ ውስጥ የሚዋኝ እና ከውሃ ውስጥ ሲወጣ መንቀሳቀስ የሚሳነው ሳይሆን እንደ ኤሊ በውሃ ውስጥ የሚዋኝ በአሸዋ ውስጥ ደግሞ የሚራመድ ፓርቲ ነው ብለዋል፡፡

ብልፅግና በፈተና ውስጥ ሃሳብ እያፈለቀ ወደ አሸናፊነት የሚጓዝ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ÷ፓርቲው የምናስበው አላማ እንዲያሳካም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በከፍተኛ ቅርበት መስራት ያስፍልጋል ነው ያሉት፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳብ ይዘው በመምጣት መታገል እንዳለባቸው ጠቁመው፥ ይሁን እንጂ ስህተትን እየፈለጉ ብሄርን ከብሄር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት እንዲሁም ሰውን ከሰው የሚያጋጩ መሆን እንደሌለባቸው ጠቁመዋል፡፡

አካታች አገራዊ ምክክርን በተመለከተ ብልፅግና እና መንግስት ከፍተኛ ፍላጎት ያለው መሆኑ ታውቆ÷ ሁሉም ከምክክሩ ኢትዮጵያን የሚያጸና ሃሳብ እንዲወለድ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ጉባኤው ወሳኝ የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የሰላም ፣ የመልካም አስተዳደር እና የእኩልነት አቅጣጫዎች የሚወሰኑበት እንደሆነ እምነታቸው መሆኑንም ነው የፓርቲው ፕሬዚዳንትና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የገለጹት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.