Fana: At a Speed of Life!

በሀሰተኛ ቼክ ከ60 ሚለየን ብር በላይ ከባንክ ሊያወጡ በሞከሩ ሰዎች ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዐቃቤ ህግ ሐሰተኛ ቼኮችን እና የክፍያ ማረጋገጫ ደብዳቤዎችን በመጠቀም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተለያዩ ቅርንጫፎች ከ60 ሚለየን ብር በላይ ሊያወጡ በሞከሩ የባንክ ሰራተኞች እና ግብረአበሮቻቸው ላይ ክስ መሰረተ፡፡
 
በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄነራል ዐቃቤ ሕግ ከፖሊስ ጋር በመሆን ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ አጠናቋል፡፡
 
በምርመራው ሪፖርትም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ ከሚሳተፈው እና በቀድሞ የሳሊኒ ኮንስትራክሽን በአሁኑ ዊቢውልድ ኢትዮጵያ ተብሎ ከሚታወቀው ድርጅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ውስጥ በድርጅቱ ስም ሀሰተኛ ቼኮች እና የክፍያ ማረጋገጫ ደብዳቤዎችን በማዘጋጀት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጅግጅጋ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ የባንኩ ቅርንጫፎች ይዘው በመቅረብ በድምሩ ብር 62 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ወጪ ለማድረግ በሞከሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጅግጅጋ ዲስትሪክት የዲጅታል ባንኪንግ ስራ አስኪያጅን ጨምሮ በወንጀል ድርጊቱ ተሳትፎ በነበራቸው 6 ተከሳሾች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቷል፡፡
 
ክሱም የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ቀርቦ አራት ተከሳሾች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ የዐቃቤ ህግን ምላሽ ለመጠባበቅ እና ሌሎች ቀሪ 2 ተከሳሾች ደግሞ መቃወሚያቸውን ይዘው እንዲቀርቡ በሚል ችሎቱ ለመጋቢት 05 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ከፍትህ ሚኒሰቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.