Fana: At a Speed of Life!

ስለአዲሱ  የኤክሳይዝ ታክስ ለህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ይሰጣል ተባለ  

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 17 ፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ)በአዲሱ ኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ዙሪያ ለከህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንደሚሰጥ የገቢዎች ሚኒስቴር  አስታወቀ፡፡

አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ ምክንያት በማድረግ አንዳንድ አካላት አላስፈላጊ ዋጋ ለመጨመር ሲንቀሳቀሱ ይታያል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው÷ ህብረተሰቡ የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለበትና ከታክስ ነፃ የሆኑ ዕቃዎችን በመረዳት ያላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ከሚያደርጉ አካላት ሊጠነቀቅ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

የኤክሳይዝ ታክስ  የተወሰኑ ዕቃዎች በሚመረቱበት፣ በሚሸጡበት ወይም ጥቅም ላይ በሚውሉበት ጊዜ የሚከፈል ታክስ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያም በተመረቱ ወይም ወደ ሀገር በሚገቡ የተመረጡ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ላይ የሚጣል ቀጥተኛ ያልሆነ ታክስ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም የኤክሳይዝ ታክስ የሚጣልባቸው ዕቃዎች እና አገልግሎቶች፡- የቅንጦት ዕቃዎች ፣ጉዳት የሚያስከትሉ ዕቃዎች እና  ፍጆታቸው የማይቀንስ ዕቃዎች  መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የኤክሣይዝ ታክስ የሚጣልበት ምክንያት ገቢ ለመሰብሰብ፣ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ፣ባለሀብቶች ከሚጠቀሙባቸው የቅንጦት ዕቃዎች ታክስ በመሰብሰብ ሰፊው ህብረተሰብ የሚጠቀምባቸውን የልማት ሥራዎች ለመሥራት ዋነኞቹ  ናቸውም ነው የተባለው፡፡

ከአሽከርካሪ ጋር በተያያዘም መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የሚጠቀሙበት ከ1ሺ3መቶ  ሲሲ በታች የሆኑ አዲስ መኪና በአውሮፓ ዘመን አቆጣጠር ከ2018 በኃላ የተሰሩ ከ35 በመቶ ወደ 5 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ እንዲቀንስ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡

ስለሆነም በቀጣይ  የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸው ዕቃዎች እና ነፃ የተደረጉ እቃዎች ለህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንደሚሰጥ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ  ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ግለሰቦች በሁሉም እቃዎች ላይ ኤክሳይዝ ታክስ እንደተጣለ አስመስለው ያላግባብ ዋጋ የጨመሩ መኖራቸውን ጠቁመው፣ በእነዚህ አካለት ላይ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወስድ አቶ ዘመዴ መግለጻቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ  ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.