Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት 6 ሚሊየን ብር የሚገመቱ የማሰልጠኛ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ዓረብ ሀገራት ለሥራ የሚሄዱ ሠራተኞችን ለማሰልጠን የሚረዱ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የማሰልጠኛ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ  እንደገለጹት፥ መንግስት የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን የማመቻቸት ስራ  በትኩረት እያከናወነ ነው።

ዜጎች ወደ መካከለኛው ምስራቅ ዓረብ ሀገራት ለሥራ ከመሰማራታቸው በፊት ተገቢው እውቀትና ክህሎት ኖሯቸው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

ድጋፉ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማትን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥  የቁሳቁሶቹ ዓይነት 24 መሆኑንም አመልክተዋል።

ቁሳቁሶቹ  በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ያላቸውን እምነት ገልጸው ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ቁሳቁሶቹ ለ16 ማሠልጠኛ ማዕከላት አገልግሎት የሚውሉ መሆኑን ከሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የአለም ዓቀፍ የፍልሰት ድርጅት የፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ማላንቦ ሞንጋ በበኩላቸው፥ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር መስራታቸው እንደሚያስደስታቸውና በቀጣይም በሚቀርቡ ፍላጉቶች መሰረት የማሰልጠኛ ቁሳቁሶችን፣ የአቅም ግንባታና የስልጠና ድጋፎችን እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.