Fana: At a Speed of Life!

የእንቅልፍ እጥረት እና ያልተስተካከለ አመጋገብ ሴቶችን ለልብ የጤና ችግር ያጋልጣል – ጥናት

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የእንቅልፍ እጥረትና ያልተስተካከለ የአመጋገብ ስርዓት ሴቶችን ከልብ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ ችግር እንደሚያጋልጣቸው አንድ ጥናት አመላከተ።

በአሜሪካ የተደረገውና ከሰሞኑ ይፋ የሆነው ጥናት የእንቅልፍ እጥረትና ያልተስተካከለ የአመጋገብ ስርአት ከመጠን በላይ ውፍረት ከሚያስከትለው ጉዳት በተመጣጣኝ ደረጃ በሴቶች ላይ የጤና እክል እንደሚፈጥር ያመላክታል።

ጥናቱ ሴቶች ያለባቸው የቤት ውስጥ ጫና እና ልጆችን የመንከባከብ ሃላፊነት ለእንቅልፍ እጦት እንደሚዳርጋቸው ጠቅሷል፤ ይህ መሆኑም በዚህ ችግር የመጠቃት እድላቸውን እንደሚያጎላው አመላክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ሴቶች በዕድሜ ምክንያት መውለድ ሲያቆሙ የሚፈጠሩ ሆርሞኖች ለእንቅልፍ እጦት እንደሚዳርጓቸውም ነው በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ እና የቀዶ ህክምና ኮሌጅ የህክምና ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር ብሩክ አጋርዋል የተናገሩት።

በጥናቱ ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 76 ዓመት የሆኑ 500 ሴቶች የተካተቱ ሲሆን፥ የጥናቱ ተሳታፊዎች የእንቅልፍ እና የአመጋገብ ልምድ ላይ ክትትል ተደርጓል።

በዚህም በቂ እንቅልፍ የሚተኙት የተሻለ የካሎሪ መጠን ያለው ምግብ የሚገቡ ሆነው ተገኝተዋል።

በተቃራኒው ለእንቅልፍ መቆራረጥ የተዳረጉት ደግሞ በመጠን በርካታ የሆነ ነገር ግን የንጥረ ምግብ ይዘቱ አነስተኛ የሆነ ምግብ መመገባቸው በጥናቱ ተገልጿል።

ይህም በቂ እንቅልፍ የማያገኙት በልቶ የመጥገብ ስሜት እስከሚሰማቸው ድረስ በርካታ መጠን ያለው ግን ደግሞ ተመጣጣኝ ያልሆነ ምግብ እንዲመገቡ ያደርጋቸዋልም ብለዋል ጥናት አድራጊዎቹ።

ከልክ በላይ መጥገብ ደግሞ በመኝታ ሰዓት ጨጓራ ላይ ጫና በመፍጠር ለእንቅልፍ መቆራረጥ ይዳርጋልም ነው ያሉት ተመራማሪዎቹ።

ከዚህ ባለፈም በብዛት መመገባቸው በጊዜ ሂደት ከልክ በላይ ለሆነ ውፍረት ያጋልጣልም ነው ያሉት፤ ሁለቱም አጋጣሚዎች የልብ ህመም ተጋላጭነትን እንደሚጨምሩ በመጥቀስ።

ምንጭ፡- www.upi.com

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.