Fana: At a Speed of Life!

ETRSS-1 ሳተላይትን መቆጣጠርና መረጃ የመሰብሰብ ስራ በኢትዮጵያውያን እየተካሄደ መሆኑን ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 19 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ራሳቸውን ችለው ETRSS-1 ሳተላይትን የመቆጣጠርና መረጃዎችን የመሰብሰብ ስራ መስራት መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አቅማቸውን እንዲያሳድጉ በቻይናውያን ባለሙያዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።

ቻይና በዘርፉ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በተለያየ ጊዜ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ በዚህም ጥሩ የቴክኖሎጂ ሽግግር በመደረጉ ኢትዮጵያውያኑ የስፔስ ባለሙያዎች ስራውን በብቃት በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ከ100 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ ተጨማሪ ሳተላይት እንደሚያስፈልጋት የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፥ የኮሙኒኬሽን ሳተላይትን ጨምሮ ሌሎች ሳተላይቶችን ወደ ህዋ ለማምጠቅ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከሶስት ዓመት በኋላ በየዓመቱ አንድ ሳተላይት የማምጠቅ ዕቅድ መኖሩንም አመልክተዋል።

አሁን ኢትዮጵያ ያመጠቀቻት ETRSS-1 ሳተላይት ከአመታት በኋላ የአገልግሎት ዘመኗ ሲያበቃ ለመተካትና ሰፊ መረጃ ለማግኘት የሚያግዙ ሳተላይቶችን ማምጠቅ በመንግስት ትኩረት እንደተሰጠውም ገልጸዋል።

በመሆኑም በተለያዩ ዘርፎች መረጃ የሚያሰባስብና የተሻለ እቅም ያለው ሳተላይት ኢትዮጵያ እንዲኖራት እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር ሰለሞን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪዋ የመሬት መመልከቻ ‘ETRSS-1’ የተሰኘች 72 ኪሎ ግራም የምትመዝን ሳተላይት ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ህዋ ማምጠቋ ይታወሳል።

ሳተላይቷ ኢትዮጵያ ለግብርና ፣ ለደንና አየር ንብረት ጥበቃ፣ ለማዕድን፣ ለተፈጥሮ ሀብት ጥናትና መረጃ ለመሰብሰብ፣ መሰረተ ልማት ለመዘርጋትና ለመጠበቅ እንደምትገለገልበት መረጃዎች ያመለክታሉ።

ምንጭ፦ ኢዜአ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.