Fana: At a Speed of Life!

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተፃፈው “መደመር” መፅሃፍ ምረቃ በተለያዩ የክልል ከተሞች ተካሂዷል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተፃፈው “መደመር” መፅሃፍ ምረቃ በተለያዩ የክልል ከተሞች ተካሂዷል።

የመጽሃፉ ምርቃት ስነ ስረዓት በኦሮሚያ ክልል አዳማ፣ ጅማ፣ በምስራቅ ወለጋ ዞን ደረጃ ነቀምቴ ከተማዎች እና በሌሎች ከተሞች ነው የተካሄደው።

በነቀምቴ ከተማ እየተካሄደ ባለው የመጽሃፍ ምርቃ ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በምርቃ ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመደመር እሳቤአቸው የአለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው የሚታወስ ነው ብለዋል።

የመደመር መፅሃፍ ኢትዮጵያውያን ተደምረው አንድነቷ የተጠበቀ እና የበለፀገች ሀገር ለመፍጠር ያለው ሚና ትልቅ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በጅማ ከተማ እየተካሄደ ባለው የምረቃ ስነ ስርዓት ላይም የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የገቢዎችና ጉሙሩክ ሚኒስቴር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፥ የመደመር መፅሀፍ ምርቃት የመደማመጥና የአንድነታችን ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ባለው “መደመር” መፅሃፍ ምረቃ ላይም የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ማእከላዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋን ጨምሮ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

አቶ አዲሱ አረጋ በአዳማ በተካሄደው መድረክ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት፥ እንኳን ለ“መደመር” መፅሃፍ ምረቃ አደረሳችሁ ብለዋል።

የመደመር ፍልስፍና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ ቢሆንም ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ሰላም እና እድገት ጉልህ ሚና ያለው ነው ያሉ ሲሆን፥ በህዝቡ እንዲዳብርም ቀርቧል ብለዋል።

በተመሳሳይ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተፃፈው “መደመር” መፅሀፍ በባህርዳር፣ በጎንደርና በደብር ማርቆስ ከተሞች ተመርቋል።

በባህርዳር በተካሄደው የምረቃ ስነ-ስርአት ላይ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት፣ ነዋሪዎችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ዕድሜ ዘመኑን ሙሉ ኢትዮጵያዊነትን ሲያቀነቅን የኖረው የአማራ ሕዝብ መደመር ማለት ምን ማለት መሆኑን ያውቀዋል ብለዋል።

መደመር በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለውን አማራ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤንሻንጉል እና መሰል ማንነቶች ረስቶና ዘንግቶ ሳይሆን ከነማንነቶቻችን በጋራ ተከባብረን የምንኖርባት ሀገር እንመስርት ማለት መሆኑንም አብራርተዋል።

በተመሳሳይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ የተፃፈው “መደመር” መፅሀፍ በደብረ ማርቆስ ከተማ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በተገኙበት ተመርቋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ መፅሃፉ እንደ ሀገር በቀደሙ ዘመናት ያሳካናቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል እድገት እንዲሁም አለም አቀፋዊና ቀጠናዊ ግንኙነቶቻችን በመደመር ፍኖተ ካርታው ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር ለሚደረገው ጉዞ እንደመነሻ የሚወሰድ መሆኑን ወይዘሮ ዳግማዊት ተናግረዋል።

በጎንደር ከተማ በተካሄደው የምረቃ ስነ ስርዓት ላይም የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት፣ ነዋሪዎችና የሀይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት በሚኒስትር ማዕረግ የኢህአዴግ አደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ተፈራ ደርበው፥ መፅሐፉ ስለሀገራዊ ለውጡ በቂ ግልፅነትና መግባባት ይፈጥራል ብለዋል።

የለውጥ ሂደቱ ከውስጥም ከውጪም ከሚያስተናግዳቸው ትችቶች አንዱ ለውጡ የሚመራበት ግልፅ ፍኖተ ካርታ የለውም የሚል እንደሆነ አንስተዋል።

በተያያዘ ዜና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተፃፈው “መደመር” መፅሃፍ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እና የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

እንዲሁም የደቡብ ክልል እና የሀዋሳ ከተማ የህብረተሰብ ተወካዮችም በምረቃው ላይ ተሳትፈዋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ባደረጉት ንግግር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተፃፈው መደመር መፅሃፍ ሰውና ተፈጥሮን የሚያስታርቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላለፈው አንድ አመት ተኩል ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግል የመደመርን ሀያልነት ያሳዩበትና አምጦ የመውለድ ያህል ከባድ የሆነውን ታላቅ ስራ ሰንደው ወደ ህዝብ ለማድረስ ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ መሆኑንም ነው የገለፁት።

በተመሳሳይ “መደመር” መፅሃፍ ምረቃ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተመቋል።

በምረቃው ላይ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በአርባ ምንጭም መደመር መፅሃፍ የአዲስ አበባ የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌን ጨምሮ የደቡብ ክልል እና የጋሞ ዞን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተፃፈው “መደመር” መፅሀፍ ምረቃ በጅግጅጋ፣ በጋምቤላ፣ በሐረር እና ድሬዳዋ ከተሞችም ተካሂዷል።

በሐረሪ ክልል ሀረር ከተማ በተካሄደ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር የፕሬስ ሴክሬተሪ አቶ ንጉሱ ጥላሁንና የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በተካሄደው “መደመር” መፅሀፍ ምረቃ ስነ ስርዓት ላይም የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የመጽሃፍ ምረቃ ስነ ስርዓቱ በድሬደዋ ከተማ አስተዳዳር እየተካሄደ ሲሆን፥ በሰነ ስርዓቱ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የወቅታዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍስሃ ይታገሱ እንዲሁም የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የኦዴፓ ስራ አሰፈፃሚ ዶክተር አለሙ ስሜ የከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ የተፃፈው ‹‹መደመር›› መፅሃፍ በጋምቤላ ክልል ጋምቤላ ከተማም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ተመርቋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ፥ በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ የተፃፈው የመደመር ፍልስፍናን የሚያስረዳው መፅሃፍ ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር የመሰረተ ልማትና የከተማ ልማት አማካሪ ሚንስትር አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፥ መፅሃፉ ዓለም በፖለቲካል ኢኮኖሚ እንዴት እንደምትመራ አመላካች መሆኑን ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.