Fana: At a Speed of Life!

መደመር ያለፈውን መልካም ወረት ይዞ በመቀጠል፤ የትናንትናን ስህተት በማረም ነገን የተሻለ ለማድረግ ያልማል- ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተፃፈው “መደመር” መፅሃፍ ዛሬ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተከናወነ ስነ ስርዓት ተመረቀ።

በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ በተከናወነው የምረቃ ስነ ስርዓት ላይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ጥሪ የተደረገላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ስለ መደመር መጽሃፍ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ መደመር ያለፈውን መልካም ወረት አጥብቆ መያዝን እንዲሁም የትናንትና ስህተቶችን ማረምን፤ ነገን የተሻለ ለማድረግ ማለምን በውስጡ ያየዘ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

መደመር ወደ ብልፅግና የምናደርገውን ጉዞ ያፋጥናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ብልፅግናም መልካም ምኞትን ለልጆቻችን እንድናወርስ ያስችላል ብለዋል።

መደመር ከሀገሪቱ ባህል፣ እሴት እና ማንነት መሆኑን በመግለጽ፤ በሀገርኛ መንገድ በሀገርኛ ቋንቋ ለእኛ እንዲመች ሆኖ የተዘጋጀ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያውያን የሰው ፍልስፍና ከመተንተን እና ከመተርጎም ይልቅ የኛን ማሳደግ እና ለዓለም ማሳወቅ ይገባል ያሉ ሲሆን፥ መደመርን አንብበን ስንተችም ከማጥላላት ይልቅ ማባዛትን የሚይዝ ፍልስፍናን ይዞ መምጣት ይገባል ብለዋል።

መደመር ሰው መሆን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ መነሻውም መድረሻውም ሰው ነው፤ የሰው ልጅን አፈጣጠር በደንብ አጥንቶ የሚያውቅ ስለ መደመር በቀላሉ ሊረዳ ይችላል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ከሶሻሊዝም ጀምሮ እስከ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የነበሩ ፍልስፍናዎች የመደብ ክፍፍልን ጨምሮ በህዝብ እና በአርሶ አደሩ እንዲነገድ ያደረጉ ናቸው ያሉት ዶክተር አብይ፥ መደመር ግን ሁሉንም አቃፊ የሆነ ፍልስፍና መሆኑን አስረድተዋል።

ከኖቤል ሽልማት ጋር በተያያዘም፥ ከሰሞኑ የተሸለሙት ሽልማቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ውጤት መሆኑን ገልፀው፥ የኢትዮጵያ ህዝብ በዓለም መድረክ ያገኘውን እውቅና ማስጠበቅ አለብን ብለዋል።

በዚህ ሽልማት ምክንያት የኢትዮጵያ ስም በዓለም መድረክ ከፍ ብሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ አሁን በሰላም የተገኘውን ኖቤል በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪ እና በሌሎች ዘፍሮች እንዴት እናምጣ የሚለው ላይ እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከፓርቲ ውህደት ጋር በተያያዘም፥ የኢህአዴግ ውህደት ጉዳይ ገና በውይይት ላይ እንዳለ እና ያለለቀ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

በኢህአዴግ ውህደት ጉዳይ ጥናት የተደረገበት እና ለ1 ዓመት ከ6 ወር ገደማ ውይይት እየተደረገበት እንዳለም ገልፀዋል።

ነገር ግን አንዳንዶች የኢህአዴግ ውህደት ሀገርን የመጨፍለቅ ስራ ነው የሚል የሚያሰራጩት መረጃ ተገቢ አይደለም፤ ኢህአዴግን ውህድ ፓርቲ ማድረግ ሀገርን መጨፍለቅ ከሆነ እስካሁን ኢትዮጵያ ተጨፍልቃለች ማለት ነው ብለዋል።

በትግራይ ውስጥ የሚገኙ ብሄረሰቦች በህውሃት፤ በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ብሄረሰቦች በአዴፓ ስር እየተዳደሩ መሆኑን በምሳሌነት አንስተዋል።

ደኢህዴን ከ56 በላይ ብሄረሰቦችን የሚወክል ፓርቲ ሆኖ ክልሉን እየመራ ባለበት ሁኔታ እንዴት ኢህአዴግ አንድ ፓርቲ ሆኖ ሀገርን መምራት ያቅተዋል ሲሉም ጠይቀዋል።

ኢህአዴግ አንድ መሆን አቅቶት እንዴት አንድ ሀገር መገንባት እንችላለን ሲሉም ገልፀዋል።

መደመር የሚለው ፍልስፍና ሀገርን ያጠፋል፤ እርስ በእርስ ያጫርሳል የሚል ሀሳብን በኢህአዴግ ውህደት ውስጥ ምን አመጣው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መደመር አያዋጣም የሚል አካል ማባዛት የሚል ሀሳብ ይዞ መጥቶ ይሟገት እንጂ ሀገር ትጠፋለች ማለት ተገቢ አይደለም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አክለውም ኢህአዴግ እንዴት ይዋሃዳል ምን ስያሜ ይኖረዋል የሚለው የእኔ ውሳኔ ሳይሆን የአባላቱ ነው ያሉ ሲሆን፥ በቅርቡ ግን የደረሰበትን ለህዝቡ ይፋ እናደርጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

በመጨረሻም በዚህ መርሃ ግብር ምክንያት በሚሌኒየም አዳራሽ የኤግዚቢሽን ፕሮግራም ለተቋረጠባቸው አካላት ይቅርታን የጠየቁ ሲሆን፥ የምረቃ ስነ ስርዓቱን ያዘጋጁ አካላትንም አመስግነዋል።

በሙለታ መንገሻ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.