Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የሚስተዋለውን የሃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ለመቅረፍ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዲስ አበባ የሚስተዋለውን የሃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

ተቋሙ ፓወር ቻይና ከተሰኘ የቻይና ኩባንያ ጋር በመተባበር ችግሩን ለመቅረፍ የኤሌክትሪክ መስመሮች መልሶ ግንባታና አቅም የማሳደግ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብሏል።

ፕሮጀክቱ የኤሌክትሪክ መስመሮችን ሃይል የመሸከም አቅም የማሳደግ፣ የሀይል ተደራሽነትን የማስፋትና ያረጁ የኤሌክትሪክ መስመሮችን የማደስ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ ለ14 ሃገር በቀል ተቋራጭ ድርጅቶችና ከ630 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩም ነው የተነገረው።

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ በጀት ከ162 ነጥብ 1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ሲሆን 15 በመቶው በተቋሙ እንዲሁም ቀሪው 85 በመቶ ከቻይና መንግስት ኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድር የሚሸፈን መሆኑ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ በዋናነት የዲስትሪቢዩሽን አውቶሜሽን ሲስተም ዝርጋታ፣ የስዊቺንግ ስቴሽኖች እና የትራንስፎርመር ተከላ፣ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ማሻሻል፣ ከንዑስ ማከፋፈያ የሚመጣውን የኤሌክትሪክ ሃይል ሳይቆራረጥ ለደንበኞች ማድረስና በኤሌክትሪክ መስመሮች ሳቢያ የሚከሰቱ አደጋዎችን መቀነስን የሚያካትት መሆኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.