Fana: At a Speed of Life!

በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰላማዊና ውጤታማ የትምህርት ኮንፈረንስ እና የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በሚል ርዕስ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው።

ስልጠናውን የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ኘሬዚዳንት ዶክተር ካሳው ተገኝ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መከባበር፣ አብሮነት፣ ሰብዓዊነት፣ አስተዋይነት የሚዳብርባቸው እና የነገ ህይወት መሰረት የሚጣልባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብሄር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካዊ አመለካከት እና በጎጠኝነት አስተሳሰብ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰብዓዊነት ሲጣስ እና ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት ሲጠፋ ተመልክተናል ብለዋል።

አያይዘውም ተማሪዎች ሰላምን በመጠበቅ ሃገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ የማሸጋገር ሃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ደሊሳ ቡልቻ በበኩላቸው፥ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች በነገ ሃገር ተረካቢዎች ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እየፈጠሩ መሆኑን አንስተዋል።

ተማሪዎች ለማህበራዊ ሚዲያ ትኩረት በመስጠት ጊዜያቸውን ያለአግባብ እያጠፉ እንደሚገኙ ጠቅሰው፥ ራሳቸውን ከሐሰተኛ መረጃ በመጠበቅ ለሃገር ሰላም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው ስልጠና በ10 የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጥ ይሆናል።

በምንይችል አዘዘው

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.