Fana: At a Speed of Life!

የኤክሳይዝ ታክስ ጨምሯል በሚል   ገበያው ላይ  የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ተገቢ አይደለም- የገቢዎች ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 21 ፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አበቤ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ በአዲሱ ኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ የታክስና ቀረጥ ቅናሽ መደረጉን አስታወቁ።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ አተገባበር በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም የኤክሳይዝ ታክስ ጨምሯል በሚል ገበያው ላይ  የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ ያለው ከስግብግበነት የሚመነጭ ነው ብለዋል።

ማሻሻያው ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እንዲሁም ህብረተሰቡ ላይ አሉታዊ ጫና እንዳይፈጠር በማሰብ የተደረገ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሯ ከኤክሳይዝ ታክስ ነፃ የተደረጉ እና ቅናሽ የተደረገባቸው ምርቶችና አገልግሎቶች በርካታ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለመደገፍ ከኤክሳይዝ እና መሰል የታክስ ዓይነቶች ነፃ የተደረጉ ምርቶች ከመኖራቸው በተጨማሪ ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ቆዳና ሌጦ ላይ ተጥሎ የነበረውን 150 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ከቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ጋር በተያያዘ ኤክሳይዝ ታክስ አንዳይጣልባቸው የተደረገ ሲሆን÷ የሀገሪቱን የሚዲያ ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ለዘርፉ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ላይ ቀደም ሲል ተጥሎ የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ ከፍተኛ ቅናሽ መደረጉን ሚኒስትሯ በመግለጫው  ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ህብረሰተቡ በብዛት ለፍጆታ የሚጠቀምባቸው እንደ ዘይት ያሉ ምርቶች ላይ የኤክሳይዝ ታክስ አለመጣሉን መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.