Fana: At a Speed of Life!

በቅርቡ ከኔዘርላንድስ የተመለሰው የ18ኛው ክፍለ ዘመን ዘውድ ለጨለቆት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ተመላሽ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ ከኔዘርላንድስ የተመለሰው የ18ኛው ክፍለ ዘመን ዘውድ በትግራይ ክልል ለሚገኘው ጨለቆት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ተመላሽ እንዲሆን ርክክብ ተደረገ::

በርክክቡ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳውን ፣የፌዴራልና የትግራይ ክልል ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

የርክክብ ሥነ ሥርዓቱና ሽኝቱ በብሔራዊ ሙዚየም ቅጥር ግቢ ነው የተካሄደው።
ጠፍቶ የነበረውን የ18ኛው ክፍለ ዘመን ዘውድ የኔዘርላንድስ የውጭ ንግድ እና የልማት ትብብር ሚኒስትር ሲግሪድ ካግ ከሳምንት በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማስረከባቸው ይታወሳል።

ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ጠፍቶ የነበረው ዘውድ ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ላይ በኔዘርላንድስ ሮተርዳም ከተማ መገኘቱ የሚታወስ ነው።

ዘውዱ በኔዘርላንድስ መንግስት እና በትውልደ ኢትዮጵያዊው በአቶ ሲራክ አስፋው ትብብር ነበር ወደ ሀገር ቤት የተመለሰው::

በተስፋዬ ከበደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.