Fana: At a Speed of Life!

የጀመርነውን የለውጥ ጉዞ ለመቀላቀልና በተሻለ ፍጥነት ለማስቀጠል ዝግጁ ሁኑ- ኢ/ር ታከለ ኡማ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አዲስ ተቀጣሪ ሰራተኞች የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለመቀላቀልና በተሻለ ፍጥነት ለማስቀጠል ዝግጁ እንዲሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እንጂነር ታከለ ኡማ ተናገሩ።

የከተማአስተዳደሩ ያወጣውን የስራ ቅጥር ፈተና በላቀ ውጤት ያለፋ 8 ሺህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ልዩ ልዩ የስራ መደቦች ላይ መመደባቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

ሠራተኞቹ ባለፋት ቀናት የቅድመ ስራ ስልጠና ሲወስዱ የቆዩ ሲሆን፥ በዛሬው እለትም የስልጠናው ማጠቃለያ መድረክ በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል።

በስልጠና የማጠቃለያ መድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እንጂነር ታከለ ኡማ፥ በአንድ ጊዜ 8 ሺህ ሰራተኛን በዜሮ ዓመት የስራ ልምድ ወደ ሲቪል ሰርቪስ መቀላቀል አዲስ ባህል ነው ብለዋል።

ተቀጥሮ መስራትንና ህዝብን ከማገልገል ጋር በተያያዘ የግል ተሞክሮአቸውን ያጋሩት ኢንጂነር ታከለ፥ አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ እና አበባ የማድረግ የለውጥ ጉዞአችንን ተቀላቅላችሁ ኃላፊነታችሁን በአግባቡ በመወጣት ነዋሪያችንን አገልግሉ ብለዋል።

“የጀመርነውን የለውጥ ጉዞ ለመቀላቀል እና በተሻለ ፍጥነት ለማስቀጠል ዝግጁ ሁኑ” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

አዲስ ተቀጣሪ ሰራተኞቹ ከፊታችን ማክሰኞ የካቲት 24 2012 ዓ.ም ጀምሮ በየተመደቡባቸው ሴክተሮች ፣ ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች በመገኘት ስራቸውን የሚጀምሩ ይሆናል።

ከ20 ሺህ በላይ የ2010 እና 2011 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች መካከል የመመዘኛ ፈተናውን ያለፉ 8 ሺህ ምሩቃን በዜሮ ዓመት ልምድ ነው በተለያዩ የከተማ አስተዳደሩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተመደቡት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.