Fana: At a Speed of Life!

124ኛው የዓድዋ ድል በዓል ተከበረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 124ኛው የዓድዋ ድል በዓል ተከብሮ ዋለ።

በዓሉን ምክንያት በማድረግም በአዲስ አበባ ንጋት ላይ መድፍ ተተኩሷል።

በዓሉ በአዲስ አበባ ሚኒሊክ አደባባይ ላይ አባት እና እናት አርበኞች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተወካዮች እንዲሁም በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ አርበኞች ፉከራ እና ሽለላን በማቅረብ ለበዓሉ ድምቀትን ሰጥተዋል።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ በአድዋ ድል የከፈለችው በስዋዕትነት ከራሷ አልፎ ለአፍሪካ መትረፉን ተናግረዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ላይ እጅግ ፈታኝ ጊዜ ላይ ትገኛለች ያሉት ሊቀመንበሩ፥ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን ከጥላቻ ይልቅ መፈቃቀርን በመስበክ ሁሉም ለሀገሩ ዘብ ሆኖ ሊቆም እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዐድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን በተመለከተ ትናንት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መልዕክት ማስተላለፋቸው አይዘነጋም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመልዕክታቸው፥ ዐድዋ በየትውልዱ እየተመነዘረ ለብልፅግና ጉዟችን ልንጠቀምበት የምንችለው ትልቅ ሃብታቸን ነው ብለዋል።

አድዋ ኢትዮጵያውያን አንድም ብዙም መሆናችንን ያሳየንበት ታሪክ ነው፤ በባህል፣ በቋንቋ፣ በብሄር፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በእምነት የየራሳችን ማንነት አለን።

ይህ ማንነታችን በሀገራችን ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኝ ታግለናል፣ እንታገላለን። ከዚህ በላይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊ ያሰኘን አንድነት አለን ሲሉም ጠቅሰዋል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.