Fana: At a Speed of Life!

ሁለቱ ኮሚሽኖች ሥራቸውን ለአዲሱ የምክክር ኮሚሽን አስረከቡ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች እንዲሁም ሀገራዊ የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽኖች የሥራ ኃላፊነታቸውን እና ሰነዶቻቸውን ለአዲሱ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስረከቡ፡፡
ርክክቡ የተካሄደው÷ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎች በተገኙበት ነው፡፡
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ ኮሚሽኖቹ ብዙ ፈተናዎችን መሻገራቸውን ገልጸው÷ በቂ ክትትል እና ድጋፍ ቢደረግላቸው ካከናወኗቸው ተግባራት በላይ መስራት ይችሉ ነበር ብለዋል፡፡
በመሆኑም እነርሱ ካለፉበት ሁኔታ ትምህርት በመቅሰም ለአሁኑ የምክክር ኮሚሽን አስፈላጊው ክትትል እና ድጋፍ መደረግ እንዳለበት አፈ-ጉባዔው አስገንዝበው÷ ሀገርን ለማስቀጠል እና ለማጽናት ይቻል ዘንድም በቅንነት እና በማስተዋል በመመካከር ሕዝቡ የሚሰጠውን ውሳኔ ሁሉም አካል መቀበል ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የቀድሞዎቹ ኮሚሽኖች ያከናወኗቸውን ሥራዎች እንደመነሻ በመውሰድ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው÷ ከዚህ አንጻርም ለአዲሱ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስፈላጊው ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዋናው ኃይል የሆነው ሕዝብ በበቂ ሁኔታ በመሳተፍ ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን እንደሚጠበቅበትም ነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ አሳስበዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው÷ የወሰን እና የማንነት ተጨባጭ ችግሮች መፈታት ስላለባቸው መንግስት እነዚህን ኮሚሽኖች ማቋቋሙ ትክክል ነበር ብለዋል፡፡
በርካታ ሥራዎችን ያከናውኑ እንጂ እንዴት መሥራት አለባቸው የሚል ደንብ ባለመዘጋጀቱ ኮሚሽኖቹ ውስንነቶችን ማስተናገዳቸውን ጠቁመው÷ለአብነትም በሀገራችን ያሉ መሠረታዊ የግጭት መንስዔዎች፣ ግጭቶች እና አፈታታቸው’ የሚለውን ጥናት በማካሄድ ምክረ ሐሳቦችን ማቅረባቸውንም ተናግረዋል፡፡
በደፈናው “ኮሚሽኖቹ አልሠሩም” የሚለው ድምዳሜም ተገቢ አለመሆኑን የገለጹት አፈ ጉባኤው÷ ከዚህ በኋላ ሥራዎችን በየጊዜው መገምገም እና መከታተል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ጀምሮ ከመተው ችግር ለመውጣት ወደ ተጨባጭ ተግባር መግባት ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡
ሁለቱ ምክር ቤቶች ኮሚሽኑ ነጻነቱን ጠብቆ እንዲሰራ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው÷ የኮሚሽኖቹ አባላት በነበራቸው የስራ ዘመን ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን ሰውተው ለሀገራቸው ለፈጸሙት ተግባር አመስግነው የዕውቅና ሰርተፊኬት ሰጥተዋል፡፡
የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር ዶክተር ጣሰው ገብሬ እና የሀገራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽነር ካርዲናል ብርሀነ ኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው÷ መንግስት በቂ ድጋፍ አለማድረጉን እና ምቹ ሁኔታዎችም እንዳልነበሩ ገልጸው የተጠኑ ጥናቶች እና የተዘጋጁ ሰነዶች ተግባራዊ እንዲደረጉ እንዲሁም የተጀመሩ ሥራዎችን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ከሁለቱ ኮሚሽኖች በርካታ ልምዶችን እንደቀሰሙ ገልጸው÷ ኮሚሽኖቹ ሥራቸውን የሚያስተዋውቁበት ምቹ ሁኔታ እንዳልነበረ መታዘባቸውን አስረድተዋል፡፡
የተዘጋጁ ሰነዶችን እና ጥናቶችን በተመለከተ ግን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው በቀጣይ የሚወሰን መሆኑን ጠቁመው÷ አዲሱ ኮሚሽን በበኩሉ ሥራዎችን በየዘርፋቸው ለይቶ በአካታች መልኩ እየተዘጋጀ መሆኑንም ኮሚሽነር መስፍን ገልጸዋል፡፡
አዲሱ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን÷ በዛሬው ዕለት ሥራቸውን እና ኃላፊነታቸውን በይፋ ያስረከቡት ሁለቱ የቀድሞ ኮሚሽኖች ግን ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከተቋማዊ ባሕርያቸው አኳያም ሪፖርታቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲያቀርቡ እንደነበር ተመላክቷል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.