Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስ ከቻይና በበለጠ በሌሎች የአለም ሀገራት እየተዛመተ ነው-የአለም የጤና ድርጅት

አዲስ አበባ፣የካቲት24፣2012 (ኤፍ.በ.ሲ) በአለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ መሆኑን የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡

የቫይረሱ መነሻ በሆነችው ቻይና  የወረርሽኙ ስርጭት እየቀነሰ ሲሆን በቀረው ዓለም ግን በሽታው በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ መሆኑ  ድርጅቱ ገልጿል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ÷ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ ከቻይና ውጭ ስምንት እጥፍ ያህል አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሪፖርት መደረጉን  ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ኮሪያ ፣ ጣሊያን ፣ ኢራን እና ጃፓን የተከሰተው ወረርሽኝ ከፍተኛ  መሆኑን ጠቁመው ÷በአሁኑ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ  ስርጭት አደጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም  አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተጨማሪ 42 ሰዎች በቻይና በኮሮና ቫይረስ መሞታቸውን ይፋ መሆኑን ተከትሎ ወረርሽኙ በዓለም ዙሪያ ለህልፈት የዳረጋቸው ሰዎች ቁጥር ከ3 ሺህ ማለፉ ነው የተነገረው።

ለህልፈት ከተዳረጉት 3 ሺህ ሰዎች ውስጥ 2 ሺህ 936 የሚሆኑት የወረርሽኑ መነሻ በሆነችው ቻይና ሲሆን በኢራን 66፣ በጣሊያን 52 እና በደቡብ ኮሪያ 29 ሰዎች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

እስካሁን በአለም አቀፍ ደረጃ 90 ሺህ 936 ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸው ተነግሯል፡፡

ላቲቪያ ፣ ሳዑዲ አረቢያ ፣ ሴኔጋል እና ሞሮኮ  ቫይረሱ በሀገራቸው መከሰቱን ሪፖርት ያደረጉ አዲስ ሀገራት ናቸው።

ምንጭ፡-ሮይተርስና ቢ.ቢ.ሲ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.