Fana: At a Speed of Life!

የሰላም ሚኒስቴርና የሲቪክ ማህበራት በአጋርነት መስራት የሚያስችላቸው የትብብር ማእቀፍ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰላም ሚኒስቴርና የሲቪክ ማህበራት በአጋርነት መስራት የሚያስችላቸው የትብብር ማእቀፍ መዘጋጀቱ ተገለፀ።

በዛሬው እለትም በተዘጋጀው ማዕቀፍ ላይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የተዘጋጀው ማእቀፍ በሰላም፣ በግጭት መከላከል ፣ በምርጫና በዴሞክራሲ መስኮች ላይ ከሚሰሩ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በትብብርና በአጋርነት መስራት የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው፥ መንግስት ከዚህ ቀደም የሲቪክ ማህበራት ላይ የሚያካሂደውን አቋም መቀየሩን ገልፀዋል።

አሁን መንግስት ከሲቪክ ማህበራት ጋር በጋራ የሚሰራበት ወቅት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የሰላም ሚኒስቴርና የሲቪክ ማህበራት በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን 10 የትብብር መስፈርቶችንም በማእቀፉ አስቀምጠዋል።

ከእነዚህም ውስጥ ሰብአዊ መብት፣ የዴሞክራሲ ግንባታ፣ ሴቶችና ህፃናት፣ የህግ ማእቀፎች አተገባበርን መፈተሽ፣ የህግ የበላይነትን ማስፈን እንዲሁም ግጭት እና ግጭት አፈታት የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።

በትብብር ማዕቀፉ ላይ የሚደረገው ምክክር ከተጠናቀቀ በኋላ የሚፀድቅ ሲሆን፥ እስከ ታች ድረስ ወርዶ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑም ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.