Fana: At a Speed of Life!

ከ5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተሰረቀ የሃይል ማስተላለፊያ አሉሙኒየም ሽቦ ተያዘ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተሰረቀ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያለው የሃይል ማስተላለፊያ አሉሙኒየም ሽቦ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተሰረቀው 5 ሚሊየን 967 ሺህ ብር ግምት ያለው 15 ጥቅል የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ አሉሙኒየም ሽቦ ሲሆን ፥ ከዚህ ውስጥ 9 ያህሉ ጥቅል ተቆራርጦ ለሌላ አገልግሎት እንዲውል መደረጉም ነው የተገለጸው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ እንዳስታወቀው ፥ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የለቡ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ባደረገው ክትትል የተሰረቀው ሽቦ በወረዳ 1 ልዩ ቦታው ለቡ መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን አካባቢ በግምት ከምሽቱ 4 ሰዓት ገደማ በአንድ የብሎኬት ማምረቻ ሼድ ውስጥ ሲቆራርጡ ከተገኙ ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

ፖሊስ ይህንን መነሻ በማድረግ ባከናወነው ምርመራ የማስፋት ስራ ፉሪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ መጋዘን ውስጥ በተመሳሳይ መንገድ በርካታ የተቆራረጡ የኤሌክትሪክ ሽቦዎችን እንዲሁም ተጠቅልለውባቸው የነበሩ ቁሳቁስ መያዝ እንደተቻለና በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ 10 ግለሰቦች ከአንድ ተሽከርካሪ ጋር በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ፖሊስ ገልጿል፡፡

የኤሌክትሪክ ሽቦው ከኢትዮጵያ አሌክትሪክ አገልግሎት የተሰረቀ ስለመሆኑ በቂ ማስረጃ እንደተገኘና ይህም በባለሙያ መረጋገጡንም ነው የከተማዋ ፖሊስ ያስታወቀው፡፡

ህብረተሰቡ በመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ህዝብ እና ሃገርን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጎዱ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥበቃ ሊያደርግላቸው እና መሰል ወንጀሎች ሲያጋጥሙ ለፀጥታ አካላት መረጃ የመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጥሪውን ማቅረቡን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.