Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም ለማልማት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 1 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል በተያዘው የምርት ዘመን ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም በዋና ዋና ሰብሎች ለማልማት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በ2014/15 የምርት ዘመን 6 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብል በማልማት ከ205 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል።

ለዕቅዱ ስኬት የምርት ማሳደጊያ ግብዓት አቅርቦትና የእርሻ ማሳ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፥ በክልሉ ደጋማና በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ያለውን ሰፊ መሬት በሙሉ በመካናይዜሽን ዘዴ ለማረስ ዛሬ በይፋ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

በክልሉ በምርት ዘመኑ የመኸር እርሻ ከሚለማው መሬት ውስጥ 75 በመቶ የሚሆነው በመካናይዝድና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

አምና በኩታ ገጠም 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት መታረሱን አስታውሰው፥ በዘንድሮው የምርት ዘመን በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ፣ ከ180 ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የገብስ፣ የበቆሎና ሌሎች የጥራጥሬ ሰብሎች ምርጥ ዘር በዩኒዬኖች በኩል ለአርሶ አደሩ እየደረሰ መሆኑን አቶ ጌቱ ጠቁመዋል።

ሊያጋጥም የሚችለውን የሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ለመፍታት ከወዲሁ በአርሶ አደሩ ከ42 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.