Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል የስራ ቋንቋዎችን ቁጥር መጨመር ልሳነ ብዙ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ያስችላል-ምሁራን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል የስራ ቋንቋዎችን ቁጥር መጨመር ልሳነ ብዙ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

የሚኒስተሮች ምክር ቤት ከአማርኛ ቋንቋ ተጨማሪ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛ እና አፋርኛ የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ መወሰኑ ይታወሳል።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የቋንቋ ምሁራን እንደገለጹት፥ ተጨማሪ ቋንቋዎችን ለፌዴራል የስራ ቋንቋነት መጠቀም ሀገራዊ እንድነትን በማሳደግ ህበረ ብሄራዊነትን ያጠናክራል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም፥ የፌዴራል የስራ ቋንቋዎችን አማራጭ ማብዛት ለሀገሪቱ አንድነት ያለው ፍይዳ የላቀ መሆኑን አብራርተዋል።

ልዩነቶችን አስታርቃ ለምትሄድ ህብረ ብሄራዊ ሀገር ባህላዊና ስነ ልቦናዊ ትስስርን እንደሚያጠናክርም አንስተዋል።

በአዲስ አባበ ዩኒቨርሲቲ የብዝሃነት ተመራማሪው ዶክተር ኸይረዲን ተዘራ በበኩላቸው፥ ውሳኔው የሀገሪቱን ህብረ ብሄራዊ ቅርጽ ለመጠበቅ የሚደረጉ ጥረቶችን ማሳዳግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ውሳኔው የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክር እና አካታች ከመሆኑ ባሻገር፥በህዝቦች መካከል መተማመንና መቀራረብን ማጠናከር እንደሚያስችል አውስተዋል።

አራቱ ቋንቋዎች ድንበር ተሻጋሪ ተናጋሪ ያላቸው እንደመሆናቸው መጠን ቀጠናዊ ፋይዳቸው ጉልህ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ኸይረዲን፥ ከስራ እድል ጀምሮ በህዝቦች መካከል ያለውን ተግባቦታዊ ሂደት የሚያቀላጥፍ መሆኑን አስረድተዋል።

ምሁራኑ ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ልሳነ ብዙ ዜጋን በማፍራት ህብረ ብሄራዊነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

በሃይለኢየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.