Fana: At a Speed of Life!

በኤክሳይስ ታክስ አዋጅ አተገባበር ዙሪያ ከቢራ አምራቾች ጋር ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲሱ ኤክሳይስ ታክስ አዋጅ አተገባበር ዙሪያ እየተፈጠሩ ያሉ ብዥታዎችን ሊያጠራ የሚችል ውይይት ከቢራ አምራቾች ጋር ተካሄደ።

ውይይቱን የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ መምራታቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የዋጋ ጭማሪ እና የሰራተኛ መቀነስ የውይይቱ አጀንዳዎች ሲሆኑ፥ በመድረኩ ከቢራ አምራቾች ለተነሱት ጥያቄና አስተያየት መልስና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ከተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች መካከል የገብስ ዋጋ መጨመር በቢራ ዋጋ ላይ ጭማሪ ለመደረጉ ምክንያት መሆኑን አምራቾች ገልጸዋል።

ከመድረክ በተሰጠው ምላሽ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት የተፈጠረ በመሆኑ ከአዋጁ ጋር ግንኙት እንደሌለው ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ሚዲያዎች የዋጋ ንረት ሊያስከትል የሚችል የታክስ አዋጅ እንደሆነ አድርገው ቀድመው ዜና በመስራታቸው ለዋጋ መጨመር መንስኤ እንደሆነና ከአምራቾች በኩል የቢራ ማስታወቂያ መከልከልና የተጠቃሚው ቁጥር መቀነስ ጋር ተያይዞ ለዋጋ መጨመሩ እንደምክንያት አቅርበዋል።

ይህም ከአዋጁ ጋር እንደማይገናኝና በመንግስት በኩል የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ነው የተገለጸው።

የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ወቅት፥ የኢትዮጵያ የታክስ ምጣኔ ከአፍሪካም ሆነ ከዓለም ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያው በምርቶች ላይ ከሚያስከትለው የዋጋ ለውጥ አንጻር ነጋዴው እያደረገው ያለው የዋጋ ጭማሪ የተጋነነ በመሆኑ ለፋብሪካዎችም ሆነ ለማህበረሰቡ ስለማይበጅ ሁሉም ሀላፊነት ተሰምቶት በጋራ መስራት ይገባዋል ብለዋል።

በተለይም በገበያ ውስጥ የዋጋ ጭማሪ የሚስተዋልበት የቢራ ምርት አምራቾች ከቸርቻሪዎች ጋር በጋራ በመስራት የማስተካከል ሃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰው፥ ኃላፊነታቸውን በማይወጡ አካላት ላይ መንግስት ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግም ነው ያነሱት።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ የቢዝነስ አመችነትን እየተገበረች በመሆኗ አሁን እየተተገበረ ያለው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ በመሆኑ አምራቾች ለሚያጋጥሟቸው ችግር በጋራ በመወያየት መፍትሄ እየሰጡ መሄድ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

አሁን እየታየ ላለው የዋጋ ንረትም ፋብሪካዎች ሀላፊነት ወስደው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰዋል።

የንግድ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ እሸቴ አስፋው አዲስ የተተገበረው የኤክሳይስ ታክስ በሌሎች ሀገራት በተለያዩ ምርቶች ላይ የተጣለውን የታክስ ምጣኔ ከፍተኛ ነው ወይ የሚለውን በሚዛናዊነት መመልክት እንደሚገባ አንስተዋል።

በአዋጁ አተገባበር ዙሪያ ግልጽነት ለመፍጠር ከሌሎች አምራቾች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ቀጣይነት እንደሚኖራቸው በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

በመጨረሻም ለአዋጁ አተገባበር ክትትል፣ ድጋፍና ቁጥጥር ለማድረግ ከሶስቱም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ከአምራቾች የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሟል።

ለሚያጋጥሙ ችግሮች በየደረጃው የተቋቋመው ኮሚቴ በየሳምንቱና በየወሩ ተገናኝቶ መፍትሄ እንዲያስቀምጥም መግባባት ላይ ተደርሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.