Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት ዳግም ወረራ ለመፈፀም እያደረገ ያለው ዝግጅት በፀረ ሕዝብነቱ መቀጠሉን ያረጋገጠ ተግባር ነው – አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በትግራይ አጎራባች ክልሎች ዳግም ወረራ ለመፈፀም እያደረገ ያለው ዝግጅት ከስህተቱ አለመማሩንና በፀረ ሕዝብነቱ መቀጠሉን የሚያረጋግጥ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘው ተሻገር ተናገሩ፡፡
ለትግራይ ክልል ሕዝብ ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዳይሆን አሸባሪ ቡድኑ ለማስተጓጎል የሚያደርገውን ሰብአዊነት የጎደለው ተግባር እንዲያቆም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አገኘው ተሻገር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ አሸባሪው ህወሓት “እኔ ብቻ የማልመራት ኢትዮጵያ ትፍረስ” ብሎ በመነሳት በሕዝቦች ትግል እውን የሆነውን ለውጥ ለማደናቀፍ እየጣረ መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪ ቡድኑ ለዳግም ጦርነት በግልጽ እየተዘጋጀ መሆኑን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር እያጋለጡ መሆኑን ጠቅሰው÷ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል እወርዳለሁ” የሚል የጥፋት አጀንዳውን ቀጥሎበታል ብለዋል።
አሸባሪው ሕወሓት የሰብአዊ ድጋፍና የግብርና ሥራ እንዳይስተጓጎል መንግስት ያወጀውን የተኩስ አቁም ለዳግም ጥፋት እየተዘጋጀበት መሆኑንም ገልጸዋል።
በአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች መንግስት የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ በማድረግ ላይ ቢሆንም÷ አሸባሪ ቡድኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች የማስተጓጎል ተግባር ስለመፈጸሙ ጠቅሰዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም የተሳለጠ ሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ ማድረግ እንዲችሉ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ አሸባሪው ህወሓት በትግራይ አጎራባች ክልሎች ዳግም ወረራ ለመፈጸም በዝግጅት ላይ መሆኑን በአደባባይ በመግለፅ ላይ ሲሆን÷ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር እያጋለጡ መሆኑን አቶ አገኘሁ ገልጸዋል።
በመሆኑም የአሸባሪ ቡድኑ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ከስህተቱ የማይማርና በፀረ ሕዝብ ተግባሩ መቀጠሉን ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች ለአርሶ አደሩ የዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት ተደራሽ በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቁመው÷ በትግራይ አካባቢ ግን ለግብርና ሥራውም ይሁን ለሰብአዊ አቅርቦቱ አሸባሪው ህወሓት እንቅፋት ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት በትግራይ ከሕጻናት እስከ አዛውንት ዜጎችን ለጦርነት እያስገደዳቸው መሆኑን ጠቁመው÷ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድርጊቱን ሊቃወመውና በግልጽ ሊያወግዘው ይገባል ነው ያሉት።
ለትግራይ ክልል ሕዝብ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረትም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊደግፈው ይገባል ብለዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.