Fana: At a Speed of Life!

ሰብዓዊነትና የሚዲያ ተቋማት ሚና ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ

 

አዲስ አበባ፣ግንቦት 10፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰብዓዊነት እና የሚዲያ ተቋማት ሚና በሚል የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከሚዲያ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዋና ጸሀፊ አቶ ጌታቸው ታኣ፥ የሚዲያ ተቋማት ቀይ መስቀል ማህበሩ ከአደጋ ምላሽ እስከ ሠብዓዊ ልማት የሚያደርጋቸውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት ስልታዊ በሆነ አግባብ እንዲታወቁ በማድረግ ሰብዓዊ ተግባሮችን ማህበራዊና አገራዊ ፋይዳ እንዲያስገኙ የሚያደርገውን ጥረት ከፍ ያደርጉታል ብለዋል፡፡

የሚዲያ ተቋማት ለቀይ መስቀል መርሆዎች መሳካት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።

በምክክር መድረኩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፥ ሰብዓዊ ምላሽ በሚፈልጉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሚዲያ የነበረው ሚና ትልቅ ነበር ነው ያሉት፡፡

ተቋማቱ ችግሮች እንዳይፈጠሩ አመላካች ስራዎችን ሲሰሩ እንደነበር ጠቅሰው፥ ሚዲያ ትልቅ ሀይል እንዳለው፣ ቀሪ ስራዎች እንዳሉ እና ምክክሩ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ÷በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት በርካታ ሰብዓዊነትን የሚፈልጉ ጉዳዮች መከሰታቸውን ጠቁመው÷መንግስት በጊዜያዊነት እና በዘላቂነት ተጎጂዎች መፍትሄ እንዲያገኙ አድርጓል ብለዋል፡፡

ቀይ መስቀል ማህበሩ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠት እየሰራ ያለውን ስራ በሚዲያ በማውጣት ትውልድን መገንባት እና መቅረፅ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

በምክክር መድረኩ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ቦርድ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ቶፊቅ አብዱላሂን ጨምሮ የሚዲያ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በፈትያ አብደላ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.