Fana: At a Speed of Life!

ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶች የመደገፍና የማብቃት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 10 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳይበር ደህንነት እና ተያያዥ ዘርፎች ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊ ወጣት ኢትዮጵያውያንን የመደገፍና የማብቃት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ገለጸ፡፡

የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛዉ እንደገለጹት÷ የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነዉ እና ETR S1KM ተብሎ የሚጠራ ሮኬት መስራት የቻለዉን ታዳጊ ሳሙኤል ዘካሪያስን የፈጠራ ሥራዎቹን ወደተሻለ ደረጃ እንዲያደርስ በአስተዳደሩ የኢትዮ-ሳይበር ታለንት ማዕከል እንዲታቀፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርም ለተማሪ ሳሙኤል ዘካሪያስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግና በዚህም የአቅም ግንባታ፣ የቁሳቁስ እና የስልጠና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የተማሪ ሳሙኤልን ተሰጥኦ ለማሳደግ በሚረዱት ጉዳዮች ላይም ዉይይት መደረጉን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በውይይቱ ተማሪው የፈጠራ ዉጤት ለሃገር የሚያበረክተዉ አስተዋጽዎ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ሹመቴ ግዛው÷ እንደ ሳሙኤል አይነት ታዳጊ የፈጠራ ባለቤቶችን አቅም በማጎልበት ለሃገር በሚጠቅም መልኩ መስራት ይገባል ብለዋል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙና በሳይበር ደህንነት እና ተያያዥ ዘርፎች ለባለ ልዩ ተሰጥኦ ታዳጊዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ራዕያቸው እንዲሳካ የራሱን ድጋፍ ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.