Fana: At a Speed of Life!

ለቀናት ብቻ የዘለቀው የአሜሪካና ታሊባን ስምምነት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አሜሪካ በአፍጋኒስታኑ ታጣቂ ቡድን ታሊባን ላይ በዛሬው ዕለት የአየር ጥቃት ፈፅማለች።

ጥቃቱ የተፈፀመው ዶናልድ ትራምፕ ከታጣቂ ቡድኑ አመራሮች ጋር ጥሩ ውይይት ማድረጋቸውን ከገለፁ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ መሆኑ ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል በአፍጋኒስታን ሰላምን ማረጋገጥ እንዲቻል አሜሪካ ባለፈው ቅዳሜ ከታሊባን ታጣቂ ቡድን ጋር ስምምነት መፈራረሟ ይታወሳል።

ይሁን እንጅ ታሊባን የተደረገውን ስምምነት ወደ ጎን በመተው በትናንትናው ዕለት በፈፀመው ጥቃት የአፍጋኒስታን መንግስት ወታደሮች ህይወት ማለፉ ነው የተገለጸው።

ይህን ተከትሎም አሜሪካ ስምምነቱን ጥሷል ባለችው የታሊባን ታጣቂ ቡድን ላይ ጥቃት መፈፀሟን የአሜሪካ ጦር ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

አሜሪካ ከታሊባን ጋር ግጭቶችን ለመቀነስ የሚያስችል ስምምነት ማድረግ መጀመሯን ተከትሎ በታጣቂ ቡድኑ ላይ ጥቃት መፈፀም አቁማ ነበር ተብሏል።

ሆኖም ቡድኑ ባለፈው ቅዳሜ ከአሜሪካ ጋር የተደረሰውን እና ብዙዎች ትልቅ ተስፋ ጥለውበት የነበረውን ስምምነት በመጣስ ጥቃቱ መክፈቱን ተከትሎ አሜሪካ ከ11 ቀናት በኋላ በቡድኑ ላይ ጥቃት ፈፅማለች።

በአፍጋኒስታን የአሜሪካ ጦር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ሶኒ ሌጌት የሀገራቸው ጦር ራሱን የመከላከል እርምጃ መውሰዱን ተናግረዋል።

አሜሪካ ለሰላም ስምምነቱ ዘላቂነት ዝግጁ ናት ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ሆኖም አጋሯን አፍጋኒስታን የመከላከል ግዴታ እንዳለባት አስገንዝበዋል።

ሆኖም ታሊባን የተፈፀመውን ጥቃት ለማረጋገጥም ሆነ ሃላፊነቱን ከመውሰድ መቆጠቡን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.