Fana: At a Speed of Life!

ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ዘርፍ እያከናወነ ያለው ተሳትፎ ማደጉና የስራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ዘርፍ እያከናወነ ያለው ተሳትፎና ተነሳሽነት እያደገ እና የስራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን የዳያስፖራ ኤጀንሲ ገለጸ፡፡

ኤጀንሲው “ከኢድ እስከ ኢድ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት” ጥሪን ተከትሎ ከኖርዌይና አቡዳቢ ከመጡ የዳያስፖራ አባላት ጋር በዘላቂ የዳያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ተወያይቷል፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ በነዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ ዳያስፖራው ከድጋፍ ባሻገር በዘላቂ ሀገራዊ ልማት ላይ ለመሳተፍ የሚያደርገውን ጥረት ኤጀንሲው ያበረታታል፡፡

ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ዘርፍ እያከናወነ ያለው ተሳትፎ እያደገና የስራ ዕድሎችን እየፈጠረ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷ አባላቱ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ያሳዩት ተነሳሽነት የሚደነቅ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የዳያስፖራ አባላት በበኩላቸው÷ በዘላቂ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ሀገራቸውንም ሆነ ራሳቸውን ለመጥቀም መስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

በግብርናና ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራት የሚችሉበት ዕድል ቢመቻችላቸው የኢትዮጵያን ምርቶች ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግና የስራ ዕድሎችን መፍጠር እንችላለን ማለታቸውን ከዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በቀጣይ ለስራቸው ስኬታማነት የሚያስፈልጉ መረጃዎችን ለማቅረብም ሆነ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለማስተሳሰር ዝግጁ መሆኑን የዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.