Fana: At a Speed of Life!

በአሜሪካ በተከሰተ ከባድ አውሎ ነፋስ የ25 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በአሜሪካ ቴኔስ ግዛት ናሽቪሌ ከተማ በተከሰተ ከባድ አውሎ ነፋስ አደጋ 25 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው ተሰምቷል፡፡

ከዚህ ባለፈም አደጋው ከ150 በላይ በሚሆኑ ዜጎች ላይ ከባድ እና ቀላል ጉዳት ማድረሱን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

እንዲሁም በብዙ መኖሪያ ቤቶች እና ሕንፃዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ነው የተገለጸው።

አውሎ ነፋሱ በእኩለ ሌሊት ሰዎች በእንቅልፍ ውስጥ በነበሩበት ሰዓት መከሰቱ አደጋውን በቀላሉ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳደረገው ተገልጿል።

አብዛኛዎቹ ጉዳቶች የደረሱት ፑትናም አውራጃ ከናሽቪል በስተምሥራቅ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከመሃል ከተማው ስምንት ማይል ርቀት ላይ በሚገኘው ጆን ካን አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ነው የተባለው።

አደጋውን ተከትሎ ትምህርት ቤቶችና ፍርድ ቤቶች ሲዘጉ የትራንስፖርት አገልግሎትም ተቋርጧል ነው የተባለው።

ከዚህ በተጨማሪም 44 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባቸዋል።

የናሽቪሌ ከተማ ከንቲባ ጆን ኮፐር በአደጋው ለተጎዱ የመጠለያ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው አደጋው ከፍተኛ በመሆኑ ዜጎች ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የነፍስ አድን ሰራተኞችን በስፍራው በማሰማራት የተጎዱ ዜጎችን የማፈላለጉ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ክስተቱን ተከትሎ አርብ ዕለት አካባቢውን ለመጎብኘት ማቀዳቸው ተነግሯል፡፡

ምንጭ፡-ቢ.ቢ.ሲ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.