Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ 218 የንጹህ ውሃና የሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በቁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ውሃ መስኖና ማእድን ልማት ቢሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 218 የንጹህ መጠጥ ውሃና የሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገለጸ፡፡

በውሃ ፕሮጀክቶቹ ከ411 ሺህ 788 በላይ የክልሉ ህዝብ ተጠቃሚ መሆኑን ቢሮው ጠቅሶ ከተጀመሩ ረጅም አመታት ያስቆጠሩና የህዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡

የክልሉ ውሃ መስኖና ማእድን ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊና የመጠጥ ውሃ አቅም ግንባታና የተቋማት አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ ኢንጂነር ፍጹም መኩሪያ÷ የንጹህ ውሃ ፕሮጀክቶቹ ከመንግስት፣ከለጋሾችና ከብድር በተገኘ ከ3 ነጥብ 45 ቢሊየን ብር በላይ እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸው ከተጠናቀቁት የውሃ ፕሮጀክቶች መካከልም 216 የሚሆኑት በገጠር የሚገኙ ሲሆኑ 2ቱ ደግሞ የከተማ ፕሮጀክቶች ናቸው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የክልሉ የንጹህ ውሃ ሽፋን በገጠር 48 ነጥብ 6 በከተማ ደግሞ 56 ነጥብ 2 ከመቶ መድረሱን ምክትል ቢሮ ሃላፊው አስረድተው አማካይ የክልሉ የንጹህ ውሃ ሽፋንም እስከ 47 ከመቶ በቅርቡ እንደሚደርስ መጠቆማቸውን ከክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ቢሮው በቀሪ የበጀት ዓመቱ ወራት 20 የሚሆኑ የከተማና የገጠር የውሃና የሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተረባረበ እንደሚገኝም ኢንጂነር ፍጹም አስታውቀው የበጀት አመቱ አፈጻጸም ጥሩ ቢሆንም ከህዝብ ፍላጎት አኳያ በርካታ የሚቀሩ ስራዎች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.