Fana: At a Speed of Life!

ምርታማነትን ለማሳደግና የአፈር ለምነትን ለመመለስ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፈር አሲዳማነትን በማከም ምርታማነትን ለማሳደግና የአፈር ለምነትን ለመመለስ ባለድርሻ አካላት በግብርናው ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን በቅንጅት እንዲሠሩ ተጠየቀ፡፡
ግብርና ሚኒስቴር ከክልል ግብርና ቢሮዎች፣ ከተመራማሪዎች፣ ከባለሀብቶች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር አሳሳቢ እየሆነ በመጣው የአፈር አሲዳማነት ላይ ተወያይቷል፡፡
ምርታማነትን ለማሳደግና የአፈር ለምነት ለመመለስ ግብርናው ላይ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ከወዲሁ ካልተሰሩ ከዚህ ቀደም ከነበረው የበለጠ ከፍተኛ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችልም ተጠቁሟል።
በግብርና ሚኒስቴር የአፈር ለምነት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ሰለሞን በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት÷ የግብርና ሚኒስቴር የአፈር ለምነትን ለመመልስ ከክልሎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በርካታ ስራዎችን እየሰራ ነው፡፡
በመድረኩ ላይ የአፈር ሲዳማነት መስፋፋትን በተመለከተ እንደተገለጸው÷ በኦሮሚያ ክልል በ14 ወረዳዎች 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሔክታር እንዲሁም በአማራ ክልል ለእርሻ አገልግሎት ከሚውለው 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ሔክታር 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ያህሉ፣ በደቡብ ክልል ከሚታረሰው የእርሻ መሬት 44 በመቶ የሚሆነው እንዲሁም በሲዳማ ክልል አጠቃላይ ካለው የመሬት ስፋት 95 ሺህ ሔክታር ያህሉ መሬት በአሲዳማነት ተጎድቷል፡፡
የአፈር አሲዳማነት እጅግ አምራች ክልሎች ላይ በስፋት መከሰቱ በምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ችግር ስለሚፈጥር÷ ጉዳዩ ጊዜ ሳይሰጠው ከክልሎች፣ ከኖራ አምራች ባለሀብቶች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የአፈር ለምነትን ለመመለስ አሲዳማ አፈርን በኖራ ለማከም እየተሰራ መሆኑን አቶ ተፈራ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ለኖራ ዝግጅት የሚሆን ከናሙና አሰባሰብ ጀምሮ እስከ መጨረሻ አርሶ አደሩ ማሳ ላይ እስከሚቀላቀል ድረስ ያለውን ሂደት ከፌዴራል እስከ ክልል በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በመንግስት በኩል ያለው የኖራ አቅርቦት በቂ ባለመሆኑ ኖራ በብዛት እንዲመረት÷ የግል ባለሀብቶችን ወደ ዘርፉ በመሳብ እና ኖራ የሚገኝባቸው ቦታዎች ላይ የፀጥታ ችግር እንዳይኖር በማድረግ ስራውን ለባለሃብቱ በመስጠት የቁጥጥር ስራ በመንግሥት በኩል ቢሰራ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል ማለታቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.