Fana: At a Speed of Life!

አስተዳደሩ ከህዝቡ ጋር ተግባብቶና ተቀናጅቶ በመስራት በአጭርና በረጅም ጊዜ የሚፈቱ ችግሮችን ለይቶ እየሰራ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከህዝቡ ጋር ተግባብቶና ተቀናጅቶ በመስራት በአጭርና በረጅም ጊዜ የሚፈቱ ችግሮችን ለይቶ እየሰራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
በመዲናዋ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሲደረግ የቆየው ውይይት መድረክ መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡
በዚሁ የማጠቃለያ መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባደረጉት ንግግር÷ አመራሩ ሕዝቡን በማሳተፍ በአገር ህልውና ላይ የተጋረጡ ፈተናዎችን እንደተሻገረው ሁሉ፤ ተግባብቶና ተቀናጅቶ በመስራት በአጭርና በረጅም ጊዜ የሚፈቱ ችግሮችን ለይቶ እየተረባረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ለውጡ በርካታ ፍሬዎችን እያፈራ ያለና ተስፋ የሚጣልበት እንጂ፤ በተግዳሮቶች ብቻ የተሞላ አለመሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ÷ የከተማችን የጥንካሬ መሰረት የሃይማኖትና የማንነት ብዝሃነት መሆኑን በመረዳት ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅርንጫ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያውያን ወደ ብልፅግና በሚወስደው ትክክለኛ መንገድ ላይ መሆናችንን የተረዱ አካላት ለማደናቀፍ ዛሬም እንደ ትናንቱ ቢረባረቡም ሕዝባችንን ይዘን እንሻገረዋለን ብለዋል።

ብዝሃነታችንን ለመለያየት በሃይማኖት አክራሪነት፣ በብሄር ፅንፈኝነት እንዲሁም በሂደት እየተመለሱ የሚገኙ ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በማራገብ አገር ለማፍረስ የሚጥሩትን አፍራሽ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡

በመድረኩ በሰላም፣ በኅብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን መገንባት፣ የኑሮ ውድነትን ማቃለል፣ የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ የጋራ ጥረት ማድረግ፣ የመንግስታዊ አገልግሎት ችግሮችን በጋራ መፍታት ፣ የልማት ጥያቄዎችን መመለስና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ የሚዲያን አዎንታዊ ሚና የማጠናከር ጉዳዮች ላይ የተናጠልና የጋራ ሚና ለመወጣት የሚያስችል መግባባት ተፈጥሯ መባሉን ከአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.