Fana: At a Speed of Life!

ሕጎች ከመጽደቃቸው በፊት በቂ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ የመንግሥት አካላት የሚረቀቁ ሕጎች ሕግ ሆነው ከመጽደቃቸው በፊት በቂ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ተገለጸ።
ይህ የተገለጸው የፓርላማ ተግባራት እና ኃላፊነቶችን አስመልክቶ ለክልል ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አመራሮች፣ ለጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች እና ለሕግ ዳይሬክቶሬቶች ኃላፊዎች በሕግ አወጣጥ ሂደት እና በሕግ ረቂቅ ዝግጅት ዙሪያ እየተሰጠ ባለ ስልጠና ላይ ነው፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሕግ ጉዳዮች ጥናት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ውበት÷ በሕገ መንግስቱ መሠረት ሕግ የማውጣት እና የማመንጨት ስልጣን የተሰጣቸው አካላት የሚያወጧቸው ሕጎች ለሀገር እና ለሕዝብ የሚያስገኙትን ጠቀሜታ አስመልክቶ በቂ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሕጎች ሲረቀቁም ሆነ ሲጸድቁ ÷ ከሀገሪቱ ሕገ መንግስት ጋር እንዳይጣረስ፣ ድግግሞሽ እንዳይከሰት፣ እንዲሁም በሌላ ሕጎች ያልተካተቱ መሆናቸውን እና በሕዝብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የማያሳድሩ መሆናቸውን ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
ሕጎች ከሀገሪቱ ፖሊሲዎች እና ስምምነት ከተፈረመባቸው ዓለም አቀፋዊ ሕጎች ጋር የሚጣጣሙ እና ብሔራዊ ጥቅምን የማያሳጡ መሆን እንዳለባቸውም መዘንጋት እንደሌለበትም ነው አቶ ኤፍሬም ያነሱት፡፡
ተሳታፊዎች በበኩላቸው የሚወጡ ሕጎችን ተፈጻሚነት በተመለከተ ፓርላማው ክትትል የማድረግ ውስንነቶች እንዳሉበት አንስተዋል፡፡
ሕገ መንግስት ከፖለቲካ ሰነድነት ይልቅ የሕግ ሰነድ ተደርጎ ቢሠራበት በየጊዜው የሚወጡ ሕጎች ተፈጻሚ ይሆናሉ፥ ሕዝባዊ መሠረት ይኖራቸዋል ብለዋል ተሳታፊዎቹ፡፡
አንዳንድ የሚወጡ ሕጎች መንግሥት እና ሕዝብን ለሙስና ተጋላጭነት ስለሚዳርጉ ሕግ ሆነው ከመጽደቃቸው በፊት በትኩረት መታየት እንዳለባቸው በውይይቱ መነሳቱን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.