Fana: At a Speed of Life!

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን የሚያደርገውን ጥረት አደነቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ መንግስት በችግር ወስጥ ለሚገኙ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን የሚያደርገውን ጥረት አደነቀ፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውድ ጂባር ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ የኢትዮጵያ መንግስት በሰላም እጦትና በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

ለአብነትም በርካታ ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ወደ ትግራይ ክልል ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ይህም በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ አርዳታ ተደራሽነት ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ያሳያል ነው ያሉት፡፡

በያዝነው ሳምንት 42 የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ 13 የካቶሊክ እርዳታ ድርጅት፣ 12 የአጋር ድርጅቶች ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ 6 ነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች ከአፋር ክልል ወደ ትግራይ ጉዞ መጀመራቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊ አቅርቦቱ ያለምንም መስተጓጓል ተደራሽ እንዲሆን የወሰደውን ቁርጠኝነት አድንቀው፤ ይህም ድጋፉ ለተጎጂዎች እንዲደርስ ማገዙን አስረድተዋል፡፡

የካናዳ ዊልፍሪድ ላውሪየር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር አን ፊትዝ-ጌራልድ በቅርቡ ይፋ ባደረጉት ጥናት ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው ሰብዓዊ ድጋፍ በዋናነት ለአሸባሪው ህወሃት አመራሮችና ተዋጊዎች ተደራሽ እንደሚሆን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ጉዳዩን በሚመለከት የተጠየቁት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውድ ጂባር፥ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ አለም አቀፍ የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት እርዳታ ማካፋፈል ሂደቱ ውስጥ ምንም ሚና እንደሌላቸው ነው የሚገልጹት፡፡

የሚቀርበው የሰብዓዊ እርዳታ ሙሉ ለሙሉ ለክልሉ አመራሮች እንደሚሰጥም ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጌራልድ ካነጋገሯቸው ተፈናቃዩች መረዳታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ አቅርቦት ክምችት እየተመናመነ በመምጣቱም፤ በመጪዎቹ የሐምሌና ነሃሴ ወራት ከለጋሽ ድርጅቶች ተጨማሪ ድጋፍ ካልተገኝ ችግሩ አስከፊ ሊሆን እንደሚችል አሳስበዋል፡፡

ከዚህ ውስጥም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተፈጠረው ቀውስ እና በድርቅ ምክንያት ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ድጋፍ እንደሚሹ ጠቅሰው፤ በመሆኑም ለጋሽ አካላት ለእለት ደራሽ የሚሰጡትን ድጋፍ በእጥፍ እንዲያሳድጉ ጠይቀዋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በቅርቡ እንደገለፀው መንግስት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ያሉ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የገባውን ቃል በማክበር እየሰራ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

ለጋሽ ድርጅቶች ከዚህ በፊት ሰብዓዊ ድጋፍ በመጫን ወደ ትግራይ ገብተው ሳይመለሱ የቀሩ 1 ሺ 25 መኪኖችን ለማስመለስ ግፊት እንዲያደርጉና ወራሪው ኃይል የሚያሰራጨውን ፕሮፓጋንዳ እንዲያቆም ጫና እንዲያሳድሩም የኢትዮጵያ መንግስት ጠይቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.