Fana: At a Speed of Life!

የሲዳማ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት አመራሩ ከግለኝነትና ጥቅመኝነት ተላቆ ለሀገረ መንግሥት ግንባታው መፋጠን እንዲተጋ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አመራሩ ከግለኝነትና ጥቅመኝነት ተላቆ ለሀገረ መንግሥት ግንባታው መፋጠን እንዲተጋ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል እና የሲዳማ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ አሳሰቡ።

‘አዲስ ፖለቲካዊ እይታ፤ አዲስ አገራዊ እመርታ’ በሚል መሪ ሀሳብ የፓርቲው የመጀመሪያ ዙር ክልል አቀፍ የአመራሮች ስልጠና ዛሬ ማምሻውን በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።

በስልጠና መድረኩ ላይ አቶ አብርሃም እንደተናገሩት ፥ ፓርቲው በ1ኛ ጉባዔው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ወደ ህዝቡ በማውረድ በብቃት ተፈጻሚ ማድረግ ከአመራሩ የሚጠበቅ ተግባር ነው።

ለዚህም በየደረጃው ብቁ አመራርና ሙያተኛ ማፍራት በማስፈለጉ ስልጠናው መዘጋጀቱን ያመለከቱት ኃላፊው ፥ አንድነቱን የጠበቀ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት እየተደረገ ያለውን እንቅሰቃሴ ለማጠናከር ስልጠናው ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

ስልጠናው ኢትዮጵያ ካጋጠማት ተግዳሮት የሚያሻግር አቅም ለመፍጠር መሰናዳቱን አስረድተው ፥ አንዱ ችግር እየፈጠረ ያለው የአስተሳሰብ ብልሽት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በመሆኑም ከግል ፍላጎትና ጥቅም ባለፈ ለህዝብ ጥቅም የሚቆም አመራር መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ፥ አመራሩ ይህንን ቁመና በመላበስ ሀገረ መንግስትና ብሄረ መንግሥት ግንባታው እንዲፋጠን በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንደሚገባው አሳስበዋል።

የስልጠናው ዓላማ ፓርቲው በጉባኤው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች በብቃት የሚያስፈጽም የአመራር አቅም መገንባት መሆኑን ገልጸው፥ በመድረኩ ላይ የተለያየ ይዘት ያላቸው ሰነዶች ቀርበው ውይይት እንደሚደርግም ተናግረዋል።

ለስድስት ቀናት የተዘጋጀው ስልጠና በሁለት ዙር ተከፍሎ እንደሚሰጥ አመላክተው፥ በመጀመሪያው ዙር ከ30 ወረዳዎችና ሰባት የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከክልል ማዕከል የተውጣጡ 1 ሺህ 280 አመራሮች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.