Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ከ4 ሺህ 500 በላይ ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል – የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሞኑን በተካሄደ የሕግ ማስከበር ዘመቻ በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ከ4 ሺህ 500 በላይ ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ዳሳለኝ ጣሰው በሰጡት መግለጫ÷ መንግሥት የክልሉን ዘላቂ ሰላም የማስጠበቅ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

እስካሁን ድረስ በተሰራው የሕግ ማስከበር ሥራ በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ከ4 ሺህ 500 በላይ ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል ነው ያሉት።

መንግሥት የክልሉን ዘላቂ ሰላም የማስጠበቅ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኃላፊው በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

ትክክለኛውን የፋኖ ስም የማይወክሉ፣ በፋኖ ስም ተደራጅተው በሕዝብ ላይ የተለያዩ ሕገ ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ቡድኖችን መንግሥት እንደማይታገስም አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል።

ትክክለኛ የፋኖ አባላትን በመንግሥት መዋቅር ሥር በማድረግ እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊው አስታውቀዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል፡፡

ጠላት ለዳግም ወረራ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ከውስጥ እና ከውጭ የጠላትን ተልዕኮ ወስደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩና በፍርድ ቤት ተፈርዶባቸው በሽብርተኛው ህወሓት ወረራ ወቅት ከማረሚያ ቤት ያመለጡ እና በተለያዩ ሕገወጥ ድርጊቶች የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን መንግሥት በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ነው ኃላፊው ያነሱት፡፡

በተወሰደው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ ከ4 ሺህ 500 በላይ ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር እንደዋሉም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ውሥጥ 210 በነፍስ ግድያ ተጠርጥረው ተከሰው የምርመራ ሂደቱ ለሕልውና ዘመቻው ቅድሚያ በመስጠት ሳይታይ የቆየ፣ ከ40 በላይ ተጠርጣሪዎች ደግሞ በፍርድ ቤት ተፈርዶባቸው በሽብርተኛው ህወሓት ወረራ ወቅት እና በተለያዩ ምክንያቶች ከማረሚያ ቤት ያመለጡ፣ ከ39 በላይ ተጠርጣሪዎች በግድያ እና በልዩ ልዩ ወንጀሎች ተከሰው በሌሉበት ተፈርዶባቸው የነበሩ እንዲሁም ከ917 በላይ ከውስጥ እና ከውጭ ተልዕኮ ሲቀበሉ የነበሩ ጸጉረ ልውጦች ሲሆኑ የመጡበት ዓላማ እየተጣራ እንደሚገኝም ኃላፊው አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ከ1 ሺህ 780 በላይ ሕዝባዊ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ፣ በልዩ ልዩ ወንጀል በመሳተፍ ጭምር የተጠረጠሩ፣ በጸጥታ መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አባላትም በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተጠቅሷል፡፡

የክልሉ ሰላም እጦት እንዲባባስ፣ ከክልሉ ውስጥ እና ከክልሉ ውጭ ተልዕኮ ተቀብለው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲሠሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎችም ተይዘዋል ብለዋል፡፡

ኃላፊው በመግለጫቸው የተለያዩ ወንጀሎችን እየሠሩ በእውነተኛው ፋኖ ስም የሚነግዱ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ሲውሉ ከእውነተኛ ፋኖ ጋር በማስተሳሰር ሥም የሚያጠለሹ ግለሰቦች እና ቡድኖች ተቀባይነት የላቸለውም ነው ያሉት፡፡

ትክክለኛ ለሀገር የቆመውን ፋኖ በማደራጀት እና በማሰልጠን በመንግሥት አደረጃጀት ስር ሆኖ ለክልሉ አንድ አቅም እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል በመግለጫቸው፡፡

የተጀመረውን የጦር መሳሪያ ምዝገባ በተመለከተ ኃላፊው በክልሉ ነዋሪው ያለውን የጦር መሳሪያ ሕጋዊ አድርጎ የሀገሩን ሰላም እንዲጠብቅ መንግሥት የጦር መሳሪያ ምዝገባ ፈቅዶ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ምዝገባው እስከ ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድም ነው የገለጹት።

ምዝገባው እንደተጠናቀቀም የትጥቅ አያያዝ እና አጠቃቀም ሕግን አስመልክቶ ሥልጠና እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.