Fana: At a Speed of Life!

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ምክትል አዛዥ በታጣቂዎች መገደላቸው ተነገረ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 15፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢራን አብዮታዊ ዘብ አባል እና ምክትል አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል ሰኢድ ሃዲ በመኖሪያ ቤታቸው መገደላቸው ተዘግቧል፡፡

ኮሎኔል ሰይድ ሆዳይ በኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ምክትል አዛዥ እና የውጭ ኦፕሬሽን ቡድን አባል ሲሆኑ፥ ቴህራን በሚገኘው መኖሪ ቤታቸው ውጪ መኪና ውስጥ እንዳሉ በሞተር ሳይከል በሚንቀሳቀሱ ሁለት ታጣቂዎች መገደላቸውን የሀገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል፡፡

ኮሎኔሉ በቀን ላይ አምስት ጊዜ በጥይት ተመትተው  ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን የተገደሉትም በኢራን ፓርላማ ህንፃ አካባቢ በሚገኝ እና ለወትሮው ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የኢራን አብዮታዊ ዘብ በኮሎኔሉ የተፈፀመውን የሽብር ተግባር በማውገዝ፥ ድርጊቱን የፈፀሙ አካላትን ተጠያቂ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ኮሎኔል ሰይድ ሆዳይ የኩድስ ሀይሎች ደጀን ነበር ሲል የገለፀው የኢራን አብዮታዊ ዘብ፥ ኮሎኔሉ ከኢራቅ እና ከሶሪያ ጋር በጀግንነት ተዋግተው እንደነበር አስታውሷል፡፡

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ግድያውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፥ የኢራን ኢስላሚክ ሪፐብሊክ ጠላቶች የኢራን አብዮታዊ ዘብ ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ሰይድ ሆዳይን በመግደል የክፋታቸውን ጥግ አሳይተዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እስከአሁን ድረስ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል አለመኖሩን እና የግድያው መንስኤም አለመታወቁን ቃል አቀባዩ ገልፀዋል፡፡

በአውሮፓውያኑ 2020 የኒውክሌር ሳይንቲስት የሆነው ሞህሰን ፋክሪዛዴ ከተገደለ በኋላ በቴህራን ውስጥ የተፈፀመ ሌላኛው ከፍተኛ ግድያ ስለመሆኑም አር ቲ እና ፕሬስ ቴቪ ዘግበዋል።

በ2020 መጀመሪያ ላይም የቁድስ ኃይል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ቃሲም ሱሌይማኒ አሜሪካ በባግዳድ አውሮፕላን ማረፊያ ባደረገቸው የድሮን ጥቃት መገደላቸው ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.