Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ዘጠኝ ከተሞች የቤቶች ዘመናዊ የመረጃ አስተዳደር ስርዓት ሊተገበር ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በከተማ ነዋሪዎች የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት በተያዘው ዕቅድ መሰረት በኦሮሚያ ክልል ዘጠኝ ከተሞች ዘመናዊ የመረጃ አስተዳደር ስርዓት እንደሚተገበር ተገለጸ ፡፡
ከቤቶች መረጃ አያያዝና አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚስተዋለው ክፍተት ለመሙላት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የታመነበት የቤቶች መረጃ አስተዳደር ሶፍትዌር ትግበራ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል፡፡
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የከተማና መሠረት ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ÷ በከተማ ቤቶች መረጃ አያያዝ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን በመፍታት ረገድ ይህ የመረጃ ስርዓት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡
በከተሞች ፍትሀዊ ያልሆነ የቤቶች ክፍፍል እንዲኖርና ይህም በዜጎች ዘንድ ቅሬታን በመፍጠር የመልካም አስተዳደር ምንጭ እንዲሆን ማድረጉን ገልጸው÷ ይህንን ተግዳሮት ለመፍታት ዘመናዊ የመረጃ ስርዓትን መተግበር ሚኒስቴሩ ሶፍት ዌር ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ከዘጠኙ ከተሞች ለተወጣጡ አመራሮችና ፈፃሚዎች ማብራሪያ የሰጡት በከተማና መሠረት ልማት ሚኒስቴር የቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ተወካይ አቶ ጸጋዬ ሞሼ÷ የሀገሪቱን ውስን የመንግስት ቤቶችን በአስተማማኝ መረጃ መያዝ በማስፈለጉ ሶፍትዌሩን በቀበሌ ደረጃ የሚገኙ አካላት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እንዲገለገሉበት ጠይቀዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የከተማ ቤቶችና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጉዮ ገልገሎ በበኩላቸው÷ በክልሉ ከ122 ሺህ በላይ የሚገኙ የቀበሌ ቤቶችን ለመመዝገብ፣ ጥገናና እድሳት ለማድረግ፣ የኪራይ ውልን ለማከናወን፣ በተከራዮች የሚነሱ የተለያዩ ጉዳዮችንና ቅሬታዎችን ለመከታተልና በወቅቱ መፍትሔ ለመስጠት የመረጃ ስርዓቱ እጅግ ጠቃሚ ነው ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.