Fana: At a Speed of Life!

የሶዶ-ዲንኬ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም 72 በመቶ ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዜ ብሔራዊ ፓርክ መዳረሻ የሆነውና በሁለት ኮንትራት ተከፍሎ በመገንባት ላይ የሚገኘው የሶዶ-ዲንኬ-ሳውላ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
የመጀመሪያው ክፍል የሆነው÷ የሶዶ-ዲንኬ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት 86 ነጥብ 22 ኪሎ ሜትር ርዝመትን የሚሸፍን ሲሆን÷ አፈጻጸሙም 72 በመቶ መድረሱ ተመላክቷል፡፡
ለግንባታውም 1 ቢሊየን 54 ሚሊየን 3 ሺህ 610 ብር ከ30 ሣንቲም መመደቡን እና ሙሉ ወጪውም በአፍሪካ ልማት ባንክ መሸፈኑን ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የዚህ መንገድ ቀጣይ ክፍል የሆነው የዲንኬ-ሳውላ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት 76 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን÷ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ የወሰን ማስከበር ችግር ከሚታይባቸው የአካባቢው አንዳንድ ከተሞች ውጪ በመልካም እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
የወሰን ማስከበር ችግሩን ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጋር በጋራ በመቅረፍ ፕሮጀክቱ ደረጃውን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል የሚጠበቅብንን ኃላፊነት እንወጣለን ሲሉ የሜላና ከተማ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት አስፋው ገልፀዋል፡፡
ለመንገዱ ግንባታ 1 ቢሊየን 20 ሚሊየን 177 ሺህ 271 ብር ከ11 ሣንቲም መመደቡን እና ሙሉ ወጪውም በአፍሪካ ልማት ባንክ የተሸፈነ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ወደ ኦሞ ኩራዝ የስኳር ፋብሪካ ለሚደረጉ ጉዞዎች አማራጭ መንገድ በመሆን ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል፡፡
እንዲሁም አካባቢው የቅይጥ ግብርና እና የእንስሳት እርባታ የሚከናወንበት በመሆኑ መንገዶቹ ተገንብተው ሲጠናቀቁ እነዚህን የግብርና ውጤቶች ሳይበላሹ በጥራትና በፍጥነት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማድረስ ያስችላሉ።
በተጨማሪም የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎንኝዎች ወደ ማዜ ብሔራዊ ፓርክ የሚያደርጉትን ጉዞ በማቀላጠፍ የአካባቢውን የቱሪስት ፍሰት ይጨምራል ነው የተባለው።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.