Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በታሪክ ትምህርት ላይ የተፈጠረውን ተቃርኖ ማረቅ እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በታሪክ ትምህርት ላይ የተፈጠረውን ተቃርኖ ማረቅ እንደሚገባ የታሪክ ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ገለጹ።
ከአንድ ዓመት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ከሰላም ሚኒስቴርና ዴስትኒ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር “ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የታሪክ ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት እና የታሪክ ኤምሬተስ ፕሮፈሰር ባህሩ ዘውዴ እንደገለጹት÷በኢትዮጵያ ሙያዊ ታሪክ አፃፃፍ የተጀመረው ከ60 ዓመት በፊት በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነበር።
የኢትዮጵያ ታሪክ ሙያዊ አፃፃፍን መከተል ከጀመረ 60 ዓመታትን ያስቆጥር እንጂ÷ በዜጎች ዘንድ ተጽዕኖ መፍጠር አልተቻለም ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ታሪክ አፃፃፍ ጉዞ፣ ለጀማሪ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለመስጠት በታሰበው የታሪክ ትምህርት፣ በታሪክ ላይ በተፈጠረው ተቃርኖና በሌሎች ታሪክ ነክ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ አመልክተዋል።
ታሪክ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የጎላ ሚና ስላለው ተቃርኖዎችን ለመፍታት የሚያስችል ኢትዮጵያን የሚወክል ታሪክ መፃፍ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች የታሪክ ትምህርት ማስተማር ቢቻልም በታሪክ አረዳድ ላይ ያለውን ልዩነት ማጥበብ እንዳልተቻለም አንስተዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ ታሪክ በትርክት እየተተካ ዜጎች የሀገራቸውን ታሪክ በትክክል እንዳይረዱ አድርጓል ብለዋል።
ትውልዱ ታሪክን በሚገባ መንገድ አውቆ ሀገርን ለማሻገር የሚያስችል የታሪክ እውቀት እንዲኖረው የታሪክ ምሁራን መምከርና ግንዛቤ መፍጠር እንዳለባቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.