Fana: At a Speed of Life!

በዩክሬን የጸጥታና ደኅንነትን ጉዳይ ላይ ሩሲያ ከማንም ጋር ለውይይት አልተቀመጠችም – ሰርጌ ላቭሮቭ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዩክሬን የጸጥታና ደኅንነትን ጉዳይ ላይ ሩሲያ ከየትኛውም ሀገር ጋር ለውይይት እንዳልተቀመጠች የሀገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ተናገሩ፡፡

ሰርጌ ላቭሮቭ ከካዛኪስታን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙክታር ትሌበድሪ ጋር ተወያይተዋል።

ከውይይቱ በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ በአሁኑ ጊዜ የሩሲያ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች የዩክሬንን ጸጥታና ደኅንነት በተመለከተ ከየትኛውም ሀገር ጋር ለውይይት እንዳልተቀመጡ ጠቁመዋል።

ከአምስት ቀናት በፊትም ለዩክሬን ላቀረብነው የሥምምነት ቅድመ ሁኔታ እና የእነርሱን አስተያየት የያዘ ምላሽ አልደረሰንም ብለዋል፡፡

ሰርጌ ላቭሮቭ ይህን ጋዜጣዊ መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት ነው የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሜር ዜሌንስኪ በፖርቹጋሉ ፓርላማ ላይ በበይነ-መረብ ቀርበው ዓለምአቀፍ አጋር ሀገራት የከባድ መሣሪያዎች ድጋፍ ማቅረባቸውን እንዲቀጥሉ ያሳሰቡት፡፡

በሌላ መድረክ ዜሌንስኪ ÷ ዩክሬን በሩሲያ በተከፈተባት ጦር ኢኮኖሚዋ በመጎዳቱ 7 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋታል ሲሉ ለዓለም ባንክና ለዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም አመራሮች መናገራቸውን ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡

እስካሁን 7 ነጥብ 7 ሚሊየን ዩክሬናውያን ከቀያቸው ሲፈናቀሉ ፣ 5 ሚሊየን ያህል ዩክሬናውያን ደግሞ ሀገራቸውን ጥለው ወደ ሌሎች ሀገራት ተሰደዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.