Fana: At a Speed of Life!

አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ከተመድ የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ጋር በተፈናቃዮች መልሶ ማቋቋም ዙሪያ መከሩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሱዚ ከሚመራ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አመራርና የአምስት ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋም በሚቻልበት ዙሪያ መክረዋል፡፡

በዚህም ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግሥት በግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና በክልሉ የሚኖሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት መልሶ በማቋቋም ረገድ የተያዙ እቅዶችን አብራርተዋል።

የተመድ ሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሱዚ የሚመራውን ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሥራ ሃላፊዎችና አምባሳደሮች፥ መንግሥት በድርቁ ለተጎዱ ዜጎችና በተፈናቃዮች መልሶ ለማቋቋም እየሰራ ላለው ሥራ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከውይይቱ በኋላ ለሶስት አመት የሚቆይ የተፈናቃዮች የዘላቂ መፍትሔ ስትራቴጂ ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል።

በፕሮጀክቱ ይፋ ማድረጊያ ስነስርዓት ላይ አቶ ሙስጠፌ መሃመድ፥ በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ማስፈን መቻሉን ጠቁመዋል።

ባለፉት ሦስት አመታት እንደ ድርቅ፣ የአንበጣ መንጋ፣ ኮቪድ 19 እና ሌሎች ተፈጥሯዊ ችግሮች ክልሉን እንደተፈታተኑ ገልፀው ይህንን ለመቅረፍ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ዋና ተጠሪና የሰብአዊ ድጋፍ አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሱዚ፥ የፕሮጀክቱ መሳካትና በክልሉ ስላሉ ተፈናቃዮች ትክክለኛ መረጃ ማግኘት መቻላቸው በክልሉ ያለው ለውጥና ቆራጥ አመራር ውጤት መሆኑን ጠቅሰው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አያይዘውም ለዘላቂ መፍትሄ ስትራቴጂው መሳካት ተመድ ያላሰለሰ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀው የፕሮጀክቱ መሳካት ለሰላምና ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የተመድ የህጻናት መርጃ ድርጅት (የዩኒሴፍ) ተወካይ ጂያን ፍራንኮ÷ ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ እሰየሰራ መሆኑን ጠቁመው ለዘላቂ መፍትሔ ተፈናቃዮችን ማሳተፍ ትልቅ ውጤት እንደሚያመጣ ተናግረዋል።

የአውሮፓ ሕብረት ተወካይ በበኩላቸው÷ ህብረቱ በድርቅና ተጓዳኝ ችግሮች የተጠቁ ዜጎችን ለመርዳት እየሰራ መሆኑን አንስተው ለፕሮጀክቱ ድጋፍ እንደሚያደርጉም አስረድተዋል።

ስትራቴጂው በአስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፎች፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰላም ግንባታ ፣በመልሶ ማቋቋም፣ በዜጎች ኑሮ ማሻሻል፣ በኢኮኖሚ ግንባታና ማህበራዊ ጉዳዮች፣ ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት በግብርናና ገጠር ልማት ፣ በመሬትና ቤቶች ልማት ላይ ትኩረቱን በማድረግ እንደሚተገበር ተገልጿል።

በፕሮጀክቱ 100 ሺህ ተፈናቃዮች ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን÷ 129 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ይደረግበታል ተብሏል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.