Fana: At a Speed of Life!

በ520 ሚሊየን ብር 23 የመስኖ ፕሮጀክቶች አዋጭነት ጥናትና ዲዛይን እየተከናወነ ነው – የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስት በተመደበ 520 ሚሊየን ብር 23 የመስኖ ፕሮጀክቶች አዋጭነት ጥናትና ዲዛይን እየተከናወነ መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ገለጸ።
በሚኒስቴሩ የጥናትና ዲዛይን ዳይሬክተር ኢንጂነር እንግዳሰው ዘሪሁን÷ መንግስት በመስኖ ልማት የያዘውን ግብ ለማሳካት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።
የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር አዳዲስ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የዲዛይን ጥናት እየተተገበረላቸው የሚገኙት ፕሮጀክቶች ትላልቅና መካከለኛ ግድቦች እንዲሁም የወንዝ መቀልበሻዎችን ያካተቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቶቹ ሁሉንም ክልሎች ያካተቱ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ÷ የአዋጭነት ጥናትና ዲዛይን እየተደረገላቸው ከሚገኙ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል የተወሰኑት በፀጥታ ችግር ቢስተጓጎሉም በተቻለ መጠን በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተጀመረውን በምግብ ራስን የመቻል ጉዞ ለማሳካት መንግስት የተለያዩ ተጨባጭ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን፥ በዘንድሮው ዓመት ብቻ በትላልቅና አነስተኛ የመስኖ ልማት የበጋ ስንዴ ሰብል በብዙ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ መሆኑ ይታወቃል።
ከሚለማው ሰብል ውስጥ 25 ሚሊየን ኩንታል ምርት የሚጠበቅ ሲሆን በቀጣዮቹ ዓመታትም ልማቱን የማስፋትና የመስኖ ግድቦችን የመገንባት ስራ እንደሚከናወን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ገልጿል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.