Fana: At a Speed of Life!

አስተዳደሩ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራትን በማጠናከር ምርትና አቅርቦታቸውን እንዲያሳደጉ ማስቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 1 ቢሊየን ብር ወጪ በማድረግ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራትን በማጠናከር ምርትና አቅርቦታቸውን እንዲያሳደጉ ማስቻሉን የከተማዋ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመጀመሪያ ጊዜ “የህብረት ስራ ግብይት ለሰላምና ለተረጋጋ የግብይት ስርዓት!” በሚል መሪ ቃል ከግንቦት 18 እስከ 21 ቀን 2014 ዓ.ም በሚያካሄደው ከተማ-አቀፍ የህብረት ስራ ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም አዘጋጅቷል፡፡

በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ የከተማው የንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ፥ ቢሮው ጤናማ የግብይት ስርዓት ለማስፈንና የግብይት ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩም ለሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ያለባቸውን የገንዘብ እጥረት እንዲቀርፉ 1 ቢሊየን ብር ወጪ በማድረግ የህብረት ስራ ማህበራትን እንዲጠናከሩ ማድረጉ ምርትና አቅርቦታቸውን እንዲያሳደጉ ማስቻሉን በመጠቆም የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የህብረት ስራ ማህበራት በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የምርት ዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት በማረጋጋት ምርቶችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተጫወቱ ያለው ተግባር የሚበረታታና በዚህ ወቅት ለወገን ደራሽ መሆናቸውንም ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉ የህብረት ስራ ማህበራት ተወካዮች በበኩላቸው ፥ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ህዝቡን ማገልገላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.