Fana: At a Speed of Life!

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ መሳተፍ የአብሮነት እና የመደጋገፍ ስነልቡናን እንደሚያሳድግ ወጣቶች ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ መሳተፍ እንደ ሀገር የአብሮነት እና የመደጋገፍ ስነ ልቡናን እንደሚያሳድግ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ገለጹ፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ፈቃደኛ ወጣቶች ፥ የበጎ ፈቃድ ተግባራት የዘመቻ ስራ ብቻ መሆን እንደማይገባቸው አንስተው ፥ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፋቸው ከራሳቸው መልካም ተሞኩሮ አልፎ ለሰዎች መልካም እንዲያደርጉ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል፡፡

አክለውም ፥ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ መሳተፍ አገልግሎቱን የሚያገኙ ማህበረሰቦችን ከመደገፍ ባለፈ እንደ ሀገር የአብሮነት እና የመደጋገፍ ስነልቡናን እንደሚያሳድግም ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በግል ስራ የሚተዳደረው ወጣት ነብዩ ሙሰማ በበጎ ፈቃደ አገልግሎት መሳተፍ ከጀመረ ስምንት ዓመታት ሆኖታል ፤ በአብዛኛው ሰዎች የደም ልገሳ እንዲያደርጉ በሚሰራው የኢትዮጰያ ወጣቶች ደም ልገሳ ማህበር ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት ይንቀሳቀሳል።

ወጣት ነብዩ በየሶስት ወሩ የደም ልገሳ የሚያደርግ ሲሆን ፥ እስካሁን ለ23 ጊዜ ያህል ደም መለገሱን ይናገራል።

በተመሳሳይ አራት ዓመታተን በዚሁ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ተሳትፎ የነበራት ሌለኛዋ ወጣት ህወት ተገኝ ደግሞ ፥ በህክምናው ዘርፍ ባለፈው ዓመት አገልግሎት ስትሰጥ የነበረች ስትሆን ፥ በወቅቱም አገልግሎት ሰጪ ሰራተኞች ከሆስፒታሉ አቅም በላይ የሚመጡ ተገልጋዮችን ለማስተናገድ እንዲሁም ተገልጋዮች ደግሞ አገልግሎት ለማግኘት ከመረጃ ማጣት እና ቋንቋ ፈተና ሲሆንባቸው መታዘብ እንደቻለች ትገልጻለች፡፡

በወጣቷ እና በሌሎች በጎ ፈቃደኞች የሚሰጡ አገልግሎቶች በበጎነት የሚሰጡ የጊዜ፣ የጉልበትና የእውቀት ድጋፎች የዜጎችን ህይወትን ለማቅለልና ለመለወጥ ያላቸውን ጉልበት የተረሩችበት እንደነበርም ነው የሚገልጹት።

በክረምት ብቻ ከተገደበው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባሻገር ዓመቱን ሙሉ በዚሁ ስራ የሚንቀሳቀሱት ወጣቶቹ ፥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የራስን ጊዜና ገንዘብ መስዋዕት በማድረግ የሚሰራ ስራ ቢሆንም፤ ለሌሎች በመድረስ፣ ሌሎችን በማገዝ የሚገኘው የህሊና እርካታና በሰዎች ላይ የሚታየው በጎ ምላሽ ትልቅ ዋጋ እንዳለው ይገልጻሉ።

ከዚህ በሻገር ለራስ ህይወት እውቀትና ልምድ ብሎም መልካም እድል የሚገኝበት አገጣሚ መሆኑን የሚያነሱት ወጣቶቹ ፥ በዚህ ዓመት በሚካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ቀድመው የጀመሯቸውን ስራዎች በማጠናከር ለመቀጠል እንዳሰቡ ገልጸዋል፡፡

ለ2014 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በአዲስ አበበባ ብቻ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ወጣቶች የሚሳተፉበት መርሐ ግብር ግንቦት 1 ቀን 2014 የተጀመረ ሲሆን ፥ ለአምስት ወራት ይቆያል በተባለው በዚህ የበጎ ስራ እንቅስቃሴ 2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የሚገመቱ የተለያዩ ስራዎች እንደሚከናወኑ የአዲስ አበበባ የህብረተሰብ ተሳትፎና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ይፋ ማድርጉ ይታወሳል።

በትግስት አብርሃም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.