Fana: At a Speed of Life!

የከተማ ግብርና አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማ ግብርና የሚገባዉን ትኩረት እንዲያገኝ የሚያስገነዝብ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሄደ፡፡

የምክክር መድረኩ በግብርና ሚኒስቴር አዘጋጅነት ከባለድርሻ አካላት ጋር የፌደራልና የክልል አመራሮች የሳተፉበት ነው፡፡

የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት ፥ በአሁን ወቅት የከተማ ግብርና ስራ ባልተማከለ መንገድ እየተሰራ እንደሆነና በከተሞች ያለዉን የምግብ ዋስትና እና የስራ አጥነት ችግሮችን ለመቅረፍ የከተማ ግብርና የሚገባዉን ትኩረት አግኝቶ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የመድረኩ አላማ የከተማ ግብርና በአመራሩ ዘንድ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ እንደሆነም ሚኒስትሩ ገልፀው ፥ የከተማ ግብርና ስራ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥና የስራ ዕድል ከመፍጠር አንፃር መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ሰነዶች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ግልፅና አስተማማኝ የሆነ የከተማ ግብርና ኤክስቴንሽን ስርዓት አለመኖር፣ የማህበረሰቡ የትኩረትና የግንዛቤ ማነስ፣ ግብዓቶች በሚፈለገው መጠን አለመገኘት፣ ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር፣ ከፌደራል እስከታችኛው መዋቅር የተናበበና ጠንካራ ትስስር አለመኖር እንዲሁም ዘርፉን የሚመጥን ግልፅ የሆነ የተጠሪነት ክፍተት መኖር ዋና ዋና ተግዳሮቶች መሆናቸው ተነስቷል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና አሳ ሃብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሳ ፥ የከተማ ግብርና ስራን ለማሻሻል ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ያለዉን እምቅ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም የድርሻቸዉን እንዲወጡና ግብርና ሚኒስቴርም ችግሮችን ለመፍታት የክትትልና ድጋፍ ስራዉን እንደሚያጠናክር ገልፀዋል።

በመጨረሻም አቶ ዑመር ሁሴን ፥ የከተማ ግብርና ስራን አመራሮች በተለይ በዚህ ወቅት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋትና የስራ አጥነት ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ በማሳሰብና ቀጣይ የመዋቅርና የቅንጅት ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም አመራሩን ጨምሮ ህብረተሰቡ ከተማ ግብርና ላይ ያለዉን ግንዛቤ ለማሳደግ የተለያዩ መድረኮችና የልምድ ልዉዉጥ ስራዎች እንደሚሰሩ በመግለፅ ቀጣይ የትኩረት አቅጣቻዎችን በማስቀመጥ መድረኩ ተጠናቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.