Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሞ ሕዝብ የገዳ ሥርዓት ውጤት የሆኑ እሴቶችን እንዲጠቀምባቸው እየተሠራ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የኦሮሞ ሕዝብ የገዳ ሥርዓት ውጤት የሆኑ ጠንካራ እሴቶችን እንዲጠቀምባቸው የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

የገዳ ስርዓት አካልና የኦሮሞ ሕዝብ ጥንታዊ የመረዳጃ ሥርዓት የሆነው ‘ቡሳ ጎኖፋ’ የተሰኘ ንቅናቄ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል፡፡

በንቅናቄ ማስጀመሪያው ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ እንደገለጹት÷ የኦሮሞን ሕዝብ የሚያጠናክሩና የሚጠቅሙ እሴቶች ሕጋዊነት ኖሯቸው እንዲተገበሩ በአዋጅ እየጸደቁ ነው ብለዋል፡፡

የዜግነት አገግልግሎት (የበጎ ፈቃድ አገልግሎት) አዋጅ ጸድቆ እየተተገበረ እንደሆነ ጠቁመው÷ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባለፉት ሰባትና ስምንት ወራት ብቻ ወደ 3 ሺህ የሚጠጉ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መሠራታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሕዝቡን ችግር ማቃለል የሚችል በቢሊየን ብር የሚገመት ሥራ መሠራት እንደተቻለም አንስተዋል።

ሌላው የገዳ ሥርዓት እሴት የሆነው ባህላዊ ፍርድ መሆኑን ጠቅሰው÷ በአዋጅ ሕጋዊ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በክልሉ ማቋቋም የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

በዚህም በርካታ ጥቅሞች እየተገኙና ሰላም የሚጠበቅበት ሥርዓት እየተተገበረ መሆኑን ተናግረው÷ ‘ቡሳ ጎኖፋ’ የተሰኘው ጥንታዊ የሕዝቡ መረዳጃና ማቋቋሚያ ሥርዓትም ሕጋዊነት ባለው መልኩ ይተገበራል ብለዋል።

‘ቡሳ ጎኖፋ’ የኦሮሞ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ሰው ሰራሽም ይሁን ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሲያጋጥሙት እርስ በርስ የሚረዳዳበት ሥርዓት መሆኑን ጠቅሰዋል።

‘ቡሳ ጎኖፋ’ በአዋጅ ተቋቁሞ ቢሮ ተደራጅቶለት እየተመራ መሆኑን የጠቀሱት የ’ቡሳ ጎኖፋ’ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ከድር÷ ሥርዓቱ በተጠናከረ መልኩ ሲተገበር ሕዝቡ ሌሎችን ሳይጠብቅ በራሱ መንገድ ከችግሩ እንዲወጣ የሚያደርግ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
‘ቡሳ ጎኖፋ’ በዋናነት ከመንግስት ከሚመደብለት በጀት በተጨማሪ ከአባላት መዋጮና ከሌሎች አካላት ድጋፍ የሚደጎም መሆኑንም አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.