Fana: At a Speed of Life!

ከአፍሪካ ጋር ያላት ትብብር በዲፕሎማሲው መስክ ሁልጊዜ ቅድሚያ የምትሠጠው መሆኑን ቻይና ገለፀች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በዲፕሎማሲዋ ቅድሚያ የምትሠጠው ከአፍሪካ ጋር በትብብር መሥራት መሆኑን የሀገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ገለጹ፡፡

ዋንግ ዪ ይህን ያሉት በቤጂንግ በተከበረው 58ኛው “የአፍሪካ ቀን” ክብረ-በዓል ላይ ነው፡፡

በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር 1963 የተቋቋመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ የሚታሰብበት “አፍሪካ ቀን” እየተከበረ ይገኛል።

ዋንግ ዪ፥ “የአፍሪካ ቀን” የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን አንድነታችንን እና ትብብራችንን የሚያንጸባርቅ የእኛም ቀን ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ፥ ቻይና እና አፍሪካ ለሉዓላዊነታቸው እና ለነጻነታቸው ብሎም ለክብራቸው መታገላቸውን አውስተው፥ በቀጣይም እርስ በእርስ በመደጋገፍ ጥቅማቸውንና የልማት ፍላጎቶቻቸውን ያሳካሉ ብለዋል፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተበት ወቅት ቻይና እና አፍሪካ ወረርሽኙን ለመቋቋም በትብብር መሥራታቸውንም አስታውሰዋል፡፡

በተጨማሪም ቻይና ለ12 ተከታታይ ዓመታት ትልቋ የአፍሪካ የንግድ አጋር ሆና መቆየቷንም ነው የተናገሩት፡፡

የ”ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ” የቻይና እና የአፍሪካ ግንኙነት ሥር እንዲሰድ ያስቻለና ውጤታማ ፕሮጀክት መሆኑንም በንግግራቸው አንስተዋል፡፡

በቀጣይም የቻይና -አፍሪካ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማደግ እንዳለበትና ትብብሩ በዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች ላይም በተግባር መንጸባረቅ እንደሚገባው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መግለጻቸውን ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.