Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት በአንጻራዊ ሰላምና መደበኛ የልማት ሥራዎች መሥራት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ነው – አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት በአንጻራዊ ሰላም እና መደበኛ የልማት ሥራዎች መሥራት በሚችልበት ሁኔታ ላይ መሆኑን የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በክልሉ የተጀመረውን የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፥ አሁን ላይ ማህበረሰቡ የተሻለ እፎይታ ያገኘበትና ከጸጥታ ስጋት የወጣበት መሆኑን ገልጸው፥ የጸጥታ ኃይሉ ሕግ የማስከበር አቅሙ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል ከአንድም ሁለት ጊዜ በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የተቃጣበት የውስጥና የውጭ ኃይሎች አደጋ የደቀኑበት እንደነበር አስታውሰው፥ ክልሉ ጎስቋላ፣ መሪ የሌለው እንዲሆንና አንገቱን እንዲደፋ የሚያደርጉ ድርጊቶች መፈጸማቸውን አንስተዋል፡፡
በአማራ ክልል እየተደረገ ያለው የሕግ ማስከበር ሥራ በቂ ምክንያት ያለው፣ ችግሮችን ለመቅረፍና የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ያለመ መሆኑን የገለጹት አቶ ግዛቸው፥ የሕግ ማስከበሩ እንቅስቃሴ የሽብር ቡድኑንና የውጭ ጠላትን ለመከላከል ለሚደረገው ዝግጅት አንደኛው አካል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ሕጻናትን ማገት፣ የተደራጀ ዝርፊያ፣ ግድያ እና ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መበራከት ክልሉን እንደፈተኑት አንስተው፥ ይህን ለማስተካከልም ሕግ ማስከበሩ አስገዳጅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተሟላ አቅም ልዩ ኦፕሬሽን በማካሄድ የሕግ ማስከበር ሥራው እየተከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት አጥፊዎችን ለማስተካከል በውይይት፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎችና በሚቀርቧቸው ሰዎች ጥረት አድርጎ እንደነበር አስታውሰው፥ በዚህ ሁሉ ያልተሳኩ ጉዳዮችን ግን በሕግ አግባብ ማስተካከል አስገዳጅ ሆኖ መገኘቱን ነው ያስረዱት።
የሕግ ማስከበሩ ዓላማ ጠንካራ ክልል የመገንባት ሂደትና ሕጋዊ የሆነ የጦር መሳሪያ አያያዝን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ገልጸው፥ በሕግ ማስከበሩ ሂደት የሚፈጠሩ ችግሮች ካሉ መንግሥት ለማስተካከል ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
ዘራፊና ወንበዴ መታረም አለበት፣ በምንም ተዓምር ፋኖ ላይ ያተኮረ እርምጃ አይወሰድም፤ በፋኖም፣ በልዩ ኃይሉም፣ በፖለቲካ መሪዎችም፣ በሃይማኖት አባቶችም ያጠፋ ይጠየቃል አንድን ወገን ብቻ የሚያጠቃ እንቅስቃሴ የለም ብለዋል፡፡
ማንኛውም ሰው ከሕግ በታች መሆኑን ማሳየት እንጂ የታገለን ፋኖ የማጥቃት ዓላማና ተግባር እንደሌለ ነው ያረጋገጡት።
“ሥርዓትና ሕግ የሚያከብሩ፣ የተጋደሉ፣ የተዋጉ ፋኖዎች አሉ፣ በእነዚህ ስም መነገድ አይቻልም፣ ማህበረሰቡ ለጀግና ፋኖዎች የሚሰጠው ክብር ይታወቃል፣ ፋኖነትን ከደሙ ጋር ያዋሀደ ጀግና ሕዝብ ነው፣ እስር ቤት ጥሶ ወንጀለኛን ያስለቀቀ ቡድን ላይ እርምጃ ስትወስድ ፋኖን ትጥቅ ሊያስፈታ ነው ይልሃል፣ ይሄ የፋኖ መገለጫ አይደለም፤ ይሄ ትልቁን ክብራችን የማዋረድና የመናቅ ነው” ብለዋል፡፡
በክልሉ እየተወሰደ ያለው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ ትልልቅ ውጤት እያመጣ መሆኑን የጠቆሙት ሀላፊው፥ ማህበረሰቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በጋራ በመሆን አጥፊዎችን እየያዘ መሆኑን ገልፀዋል። በክልሉ እየተወሰደ ያለውን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ ሕዝቡ አልደገፈውም የሚባለውም ሀሰት መሆኑን ነው የጠቆሙት።
የአማራን ሕዝብ ወዳልተገባ ብጥብጥ እንዲገባ ለማድረግ የሚጥሩ ኃይሎች አሉ ያሉት አቶ ግዛቸው፥ የአማራ ሕዝብ አስተዋይ በመሆኑ እንዳልተሳካላቸውም ተናግረዋል፡፡
“ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ማለት ሰዎችን መሳደብ አይደለም፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ማጋጨት አይደለም፣ እየተከፈለው የስለላ ሥራ መሥራት አይደለም፣ ይሄን የሚያደርግ የሃሳብ ነጻነት ሳይሆን ሕገ ወጥነት ነው” ብለዋል፡፡
በክልሉ የአማራን ሕዝብ ለሚያጠቃ ጠላት የመሳሪያ ዝውውር የሚፈጽሙ እና የአማራን ሕዝብ ለሚያጠቃው የሽብር ቡድን ነዳጅ የሚያደርሱ አካላት ስለመኖራቸውም አንስተዋል፡፡
ሰላምን በማረጋገጥ የክልሉን ልማት ማፋጠን፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ አለብን ያሉት አቶ ግዛቸው፥ የሕግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ለዳግም ወረራ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው፥ በያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች በዜጎች ላይ ከፍተኛ በደል እየፈጸመ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
“የሽብር ቡድኑ ሊያጠቃ የሚችለው የአማራ ሕዝብ አንድነት የተሸረሸረ ጊዜ ብቻ ነው፣ አማራ አንድ በሆነ ጊዜ የትኛውም፣ የውጭም የውስጥም ጠላት አማራን ሊደፍረውም፣ ሊነካውም አይችልም “ብለዋል፡፡
የክልሉ የትኩረት አቅጣጫ አንድነትን ማጠናከር መሆኑን እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል በሚገባው ልክ መደራጀቱንም አስታውቀዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.