Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 10 ወራት የሎጂስቲክስ ወጪን ለመቀነስ በተከናወኑ ተግባራት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ ማዳን መቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 10 ወራት የሎጂስቲክስ ወጪን ለመቀነስ በተከናወኑ ተግባራት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ ማዳን መቻሉን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
 
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ እያካሄደ ባለው 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባዔ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርን የ2ዐ14 በጀት ዓመት የ10 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት አድምጧል ፡፡
 
ሪፖርቱን ያቀረቡት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፥ ባለፉት 10 ወራት የሎጂስቲክስ ወጪን ለመቀነስ በተከናወኑ ተግባራት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ ማዳን መቻሉን አብራርተዋል።
 
በዚህም ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ 10 ወራት ባህርተኞችን በማሰልጠንና በውጭ አገራት መርከቦች ላይ በማስቀጠር 6 ነጥብ 75 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ገልጸው ኢትዮጵያ ባህርተኞችን ወደ ውጭ አገራት ለማስቀጠር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀቷንም አመላክተዋል።
 
እንደ ኢዜአ ዘገባ በ10 ወራቱ ከሲቪል አቪዬሽን አገልግሎት 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ለመሰብሰብ ታቅዶ 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል።
 
ሚኒስቴሩ የዕውቀት ሽግግር፣ የአቅም ግንባታን ማጠናከር እና ማስቀጠል እንዲሁም ዲጂታል የክትትል እና ግምገማ ሥርዓትን ማዳበር፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የትራንስፖርት ዘርፉን ማዘመን የሚሉ ቁልፍ ተግባራትን ለማዘመን አቅዶ እየሠራ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
 
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በ”ብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ” በ10 ዓመት ውስጥ 100 ሺህ የሚጠጉ ባህርተኞችን በማፍራት እስከ 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ማቀዱም ተጠቁሟል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ጉባኤው የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ ባቀረቡት የመንገድ ትራንስፖርት ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ የመንገድ ትራንስፖርት ረቂቅ አዋጅን በሶስት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

የጸደቀው አዋጅ ቁጥር 1274/2014 ስያሜ ተሰጥቶታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.